ለአረጋውያን ክብር፣ ፍቅር እና ዘላቂ ደህንነት በጋራ እንሥራ!

ዕድሜያቸውን፣ ጉልበታቸውን እና እውቀታቸውን ለትውልድ ማስተላለፍና ሀገርን ማፅናት ላይ ላዋሉት ውድ አረጋውያን የምንሰጠው እንክብካቤ የውዴታ ግዴታ ብቻ ሳይሆን፣ የህሊና እና የሞራል ዋጋችን መለኪያ ጭምር ነው።
‎
‎ትናንት ወራሪ ጠላትን አሳፍረው ሀገራችንን በጀግንነትና በክብር ያቆዩልን፤ ዛሬ በምናየውና በተገነባችው ሀገር ውስጥም የእጃቸውን አሻራ – የላባቸውን ጠብታ ያሳረፉ ባለውለታችን በመሆናቸው በእርጅና ዘመናቸው ፍቅርን፣ ሰላምን እና የተሟላ ክብካቤን ማግኘት ይገባቸዋል።
‎
‎የእውቀት ማህደር የሆኑት አረጋውያን በረጅም ጊዜ ያካበቱትን ሰፊ ልምድ ለወጣቱ በጥበብ በማስተማር ለትውልድ ቅብብሎሽ ቀጣይነት ድርሻቸው የላቀ ነው።
‎
‎አረጋውያንን መከባከብና ደህንነታቸውን ማስጠበቅ ማለት ያለፉትን ትውልዶች አስተዋጽዖ ማክበር እና ለወደፊቱ የራሳችን ዕድሜ ዋስትና የሚበጅ ጠንካራ መሰረት መጣል ማለት ነው።
‎
‎አረጋውያን እድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ አካላዊ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን፤ ማህበራዊ ፍቅር፣ አክብሮት እና የስነ-ልቦና መረጋጋትን አበክረው ስለሚሹ ደህንነታቸውን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሁላችንም የጋራ ሃላፊነት ሊሆን ይገባል።
‎
‎ስለሆነም በቤተሰብ ደረጃ ከጎናችን ያሉ አረጋውያንን በማወያየት፣ በመንከባከብና አርአያነታቸውን በማክበር ፍቅራችንን እናሳይ። በማህበረሰብ ደረጃም ተጋላጭ የሆኑ አረጋውያንን በመደገፍ፣ በማህበራዊ ህይወት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ እና ክብር እናስጠብቅ።
‎
‎👉 የእናንተስ አስተዋጽዖ ምንድነው❓

Please follow and like us: