Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ማህበራዊ አካታችነትና የዜጎች የላቀ ተጠቃሚነት በመደመር እሳቤ
ህብረተሰባችንን ፍትሃዊ፣ ሰብአዊ እና ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ ወደ ላቀ ከፍታ ማሻገር የሚቻለው ማህበራዊ አካታችነትን ማረጋገጥ ስንችል ነው።
የመደመር እሳቤ መሰረቱ ማግለልን አስወግዶ ሁሉንም ዜጋ በባለቤትነት ማቀፍ በመሆኑ፣ የዜጎችን የላቀ ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ ቁልፍ መሳሪያ ነው።
በመሆኑም የሁሉንም አካል ድምጽ ማሰማት፣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን ማረጋገጥ እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነት፣ ሕብረብሔራዊ አንድነትና ትስስርን የበለጠ ማጠናከር የመደመር መንግስት ትልልቅ እሳቤዎችና ዋነኛ የትኩረት ነጥቦች ናቸው።
ይህን መሠረት በማድረግም ባለፉት የለውጥ አመታት ሴቶች፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ ህጻናት እና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ዜጎች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁነቶች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ የማድረግ ስራ በሰፊው ተሰርቷል።
ማህበራዊ አካታችነትን በተግባር ከማረጋገጥ አኳያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ተቋማት ውስጥ የሴቶችን አመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ሚና ማረጋገጥ ከፆታ በዘለለ የችሎታ እና የፍትህ ጉዳይ ሆኖ በተግባር እየተተገበረ ይገኛል።
አረጋውያን የህብረተሰቡ የዕውቀትና የልምድ ማህደሮች ብሎም የሀገር ባለውለታዎች እንደመሆናቸው መጠን ተገቢውን ክብርና እንክብካቤ እንዲሁም ማህበራዊ ጥበቃና ድጋፍ እንዲያገኙ ተቋማዊ ማዕቀፎች ተጠናክረዋል።
የአካል ጉዳተኞች እና ልዩ ፍላጎት ያላቸው ዜጎችን ማዕከል ያደረገ የመሠረተ ልማት ተደራሽነትን በማስፋት፣ በሥራ ስምሪትና በትምህርት እድል ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።
የሕጻናት መብቶች ጥበቃና እንክብካቤን በተመለከተም የሕጻናትን ደህንነት የሚጠብቁ፣ አስተማማኝ መሰረት የሚጥሉ እና የወደፊት ተስፋቸውን የሚያለመልሙ ስራዎች እንደ ማህበራዊ ዋስትና መሰረት በትኩረት እየተከናወኑ ናቸው።
በእሳቤው መነሻነት የልማት ውጤቶች ወደታችኛው ማህበረሰብ ክፍል እንዲደርሱ በማድረግ ስራ አጥነትን፣ የኑሮ ውድነትን እና ድህነትን በዘላቂነት ለመቀነስ የሚያግዙ አስቻይ መደላደሎች ለመፍጠር በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል።
ልዩነቶችን እንደ ጸጋና መበልፀጊያ እድል በመጠቀም፣ በጋራ በመተጋገዝ እና በመደመር መንፈስ የሰመረችና የፀናች ሀገር ለመገንባት እና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ መንግስት ከቃል ባለፈ እየወሰደ ያለው ተግባራዊ እርምጃ ወደፊትም አጠናክሮ ይቀጥላል።

