Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ለህጻናት ሁለንተናዊ መብትና ደህንነት ዘላቂ ትኩረት!
ህጻናት የነገዋ ሀገር መሠረቶችና የትውልድ ቀጣይነት ማረጋገጫዎች እንደመሆናቸው መጠን ሁለንተናዊ ዕድገታቸው ከሀገር ዕድገት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው።
መንግስት በሀገሪቱ ህጎች ሁሉ የበላይ በሆነው ሕገ መንግስት አንቀጽ 36 እንዲሁም በብሔራዊ የህፃናት ፖሊሲ አማካኝነት የህጻናትን መብትና ደህንነት የሚያረጋግጡ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል። ይህን ለማስፈፀም ብሔራዊ የህፃናት ፖሊሲ ፀድቆ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ ውሏል።
የፖሊሲው ዋና ራዕይም የኢትዮጵያ ሕፃናት መብቶቻቸው ተከብሮና ደህንነታቸው ተጠብቆ ማየት ነው። ፖሊሲው ሕጻናት የተሟላ ስብዕና ተላብሰው እንዲያድጉ፣ መብታቸው እንዲከበርና ደህንነታቸው እንዲረጋገጥ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር መልካም ስነ-ምግባር የተላበሰ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ይሰራል።
· የሕጻናት የመኖርና በምቹ ሁኔታ የማደግ መብት፡ ማንኛውም አካል የሕጻናትን የመኖር መብት የማክበር፣ ፍላጎታቸውን የማሟላት እንዲሁም ከሞት የማዳንና በምቹ ሁኔታ የማደግ መብትን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት።
· ለሕፃናት ጥቅምና ደህንነት ቅድሚያ መስጠት፡ ቤተሰብ፣ ማሕበረሰብ፣ መንግስታዊ ወይም በጎ አድራጎት ተቋማት ሕፃናትን የሚመለከቱ ተግባራት ሲያከናውኑ ለሕጻናት መብትና ደህንነት ቅድሚያ መስጠት ይኖርባቸዋል።
· ከአድሎ ነፃ መሆንና ተሳትፎ፡ ሕፃናት በዘር፣ በሀይማኖት፣ በቋንቋ፣ በፆታ ወይም በአካል ጉዳት ዓይነት ልዩነት ሊደረግባቸው የማይገባ ሲሆን፣ ራሳቸውን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን በነፃነት ገልጸው ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረግ ይገባቸዋል።
የህጻናትን መብትና ደህንነት የማክበር፣ የማስከበር እንዲሁም ፍላጎቶቻቸውን የማሟላት ኃላፊነት የሁሉም አካል ነው።
