በጅማ ዞን እየተሰሩ ያሉ ወጣት ተኮር የግብርና ዘርፍ ልማቶች ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ያስቻለ ነው ተባለ።

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ የተመራ የልዑካን ቡድን በጅማ ዞን ሊሙ ኮሳ ወረዳ በመገኘት የተሰሩ ወጣት ተኮር የግብርና ዘርፍ ልማቶችን ጎብኘተዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ በዞኑ እየተሰራ ያለው የግብርና ልማት ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል የፈጠረ ነው ብለዋል። በግብርናው ዘርፍ በተለይም በፍራፍሬና በከብት ማድለብ ላይ ተደራጅተው የተሰማሩ ወጣቶች የጀመሩት ልማት የሚበረታታ እንደሆነ ተናግረዋል። ሚኒስትር ዲኤታዋ አክለውም በዞኑ የተመለከቱት የሙዝ ተክል ልማት፣ የወጣቶች ማእከል እና የከብት ማድለብ ተግባሪት ለወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የልማት ተሞክሮው ወጣቶችን አደራጅቶ በየዘርፉ በማሰማራት ከዚህም የበለጠ ማልማት የሚቻልበት እድል መኖሩን የሚያመላክት መሆኑን ጠቁመዋል። በጉብኝቱ የተገኙ የክልል የስራ ኃላፊዎችም በግብርናው ዘርፍ ለወጣቶች ከተፈጠሩ የስራ እድሎች የተገኙ ውጤታማ ተሞክሮዎችን በመውሰድ በክልላቸው ቢተገበር ወጣቶችን በተጨባጭ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ እንደሚረዳቸው ገልጸዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ማቲዎስ ሰቦቃ በበኩላቸው በክልሉ በተመረጡ ዞኖች የፍራፍሬ አና የከብት ማድለብ ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰሩ ነው ብለዋል። ወጣቶችን ያሳተፉ የተለያዩ የግብርና ልማት ኢኒቬተቮች በሊሙ ኮሳ ወረዳ በሙዝ በአቮካዶ በሩዝ በሻይ ቅጠል ክላስትሮች በመደራጀት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በዚህም ለወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል።

የጅማ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ የሱፍ ሻሮን በበኩላቸው በዞኑ ወጣቶች በተለያዩ የግብርና ስራዎች ተሰማርተው እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል። በጉብኝቱ የፌዴራል፣ የዞንና የወረዳ ኃላፊዎች የተገኙ እንዲሁም ከተለያዩ ክልሎች የመጡ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሀላፊዎች የሙዝ ተክል ልማት፣ የተደራጁ ወጣቶች የከብት ማድለቢያ ጣቢያ እና የዘመናዊ የንብ ቀፎዎች ተመልክተዋል።

Please follow and like us: