Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመንግስትና በማህበረሰቡ ያልተሸፈኑ የልማት ሥራዎችንና ማህበራዊ አገልግሎቶችን በማከናወን 19.3 ቢሊየን ብር የሚገመት ሀብት ማዳን መቻሉ ተገለፀ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር “በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ ” በሚል መሪ ቃል ሲያከናውን የቆየውን የ2016 ዓ.ም አገር አቀፍ የክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዛሬ ማጠቃለያውን በጅማ ከተማ አድርጓል።
በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ ክብርት ሙና አህመድ እንደገለፁት በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን 52.7 ሚሊዮን የሚሆኑ የህበረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል ፡፡ በዚህም በመንግስትና በማህበረሰቡ ያልተሸፈኑ የልማት ሥራዎችንና ማህበራዊ አገልግሎቶችን በማከናወን 19.3 ቢሊየን ብር የሚገመት ሀብት ማዳን እንደተቻለ ገልፀዋል ። ሚኒስቴር ድኤታዋ እንደገለፁት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኢትዮጵያ በብዝሃነት ያሸበረቀች ሀገር መሆኗን እንዲገነዘቡ፣ የወንድማማችነት/ እህትማማችነት እሴቶች እንዲጎለብቱ፣ ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችን እንዲጠናከር እድል የፈጠረ መድረክ መሆኑንም ጠቅሰዋል ።

የኦሮሚያ ክልል የወጣቶችና ስፓርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ማቲያስ ሰቦቃ እንደገለፁት ለአገረ መንግስት ግንባታም ሆነ የለውጥ አካል የሆኑት ወጣቶች የክልሉ መንግስት ሰፊ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ ጠቅሰው በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከዘጠኝ ሚሊየን በላይ የክልሉ ወጣቶችን ማሳተፍ መቻሉን ጠቅሰዋል ። በዕለቱ የእንኳን ደህና መጣቹ መልዕክት ያስተላለፉት የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ጣሂር ቀመር በበኩላቸው የከተማዋ ዕድገት ሁሉን ያካተተና የወጣቶችን ተሳትፎ ያረጋገጠ እንዲሆን አየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

በማጠቃለያ መርሀ ግብሩ ፣ በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዘርፎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ ውጤታማ ስራ የሠሩ ተቋማት ፣ማህበራትና አጋር አካላት የተለያዩ ዕዉቅናና ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል ።
