Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ድንበር ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ ወጣቶች ትስስርን ይበልጥ ለማጎልበት ጉልህ አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ ተገለፀ፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር በመተባበር “Volunteerism, a Bridge for Pan-Africanism” በሚል መሪ ቃል ከጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለ3 ቀናት የሚቆይ ድንበር ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሐ-ግብር በጅቡቲ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በትናንትና እና በዛሬው መርሐ-ግብር ላይ የሁለቱ አገራት ወጣቶች የጋራ ሲምፖዚየም እና የደም ልገሳ ተካሄዷል። ከድንበር ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ-ግብሩ ጎን ለጎን የጅቡቲ የወጣቶችና ባህል ሚኒስቴር ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀውና ትኩረቱን በሠላም፣ በማህበራዊ ደህንነት እና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ባደረገው ቀጠናዊ የወጣቶች ፎረም ላይ የኢትዮጵያ ልዑካን አባላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ለቀጠናው ሠላም እያበረከተችው ባለው አስተዋፅዖና በአረንጓዴ አሻራ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የወጣቶች ተሳትፎ እንዲሁም የወጣቶች አጠቃላይ ተጠቃሚነት ዙሪያ ያለውን ተሞክሮ ለሌሎች አገራት ተሳታፊዎች አጋርተዋል፡፡

ድንበር ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወንድማማችነትና እህትማማችነትን፣ ትብብርንና አጋርነትን በማጎልበት ቀጠናዊ አንድነትና ትስስርን በመፍጠር ለፓን አፍሪካኒዝም መጎልበት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ የመርሐ-ግብሩ ተሳታፊዎች ጠቁመዋል፡፡ በመርሐ-ግብሩ ላይ ከሀገራችን ኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ የፌዴራልና የክልል አመራሮች በድምሩ 60 የልዑካን ቡድን አባላት በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ከስፍራው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
