አርሜኒያ የተቋሙን ስራዎች በዲጂታል ስርዓት ለማዘመን ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንደምታደርግ ገለፀች

የኢፌዲሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የአርሜንያ አምባሳደር እንዲሁም የአፍሪካ ህብረትና የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቋሚ ተወካይ ሳክ ሳርጊሲያን ጋር ውይይት አካሂደዋል።

ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎቹ በጋራ መስራት በሚያስችሉ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ በሰፊው መክረዋል። በውይይቱ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የኢትዮ አርሜንያ ወዳጅነት ዘመናትን የተሻገረ መሆኑን ተናገረዋል። ሁለቱም ሀገራት ሰፊ የታሪክ፣ የሃይማኖት እና የባህላዊ ትውፊት ባለቤት እንዲሁም በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ መስኮችም ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አንስተዋል።

በተለይም በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲሁም አጋርነት ይበልጥ በሚጠናከርበት ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋል። በተጨማሪም በስርዓተ ፆታ እኩልነት፣ በማህበራዊ ጥበቃ፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ ጥቃትን በመከላከል ረገድ ያሉ በጎ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥና ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት በሚያስችሉ ነጥቦች ላይም በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል። በኢትዮጵያ የአርሜንያ አምባሳደር ሳክ ሳርጊሲያን በበኩላቸው፥ አርሜኒያ በተለይ በአይሲቲ ዘርፍ ያላት ሰፊ ልምድና እውቀት ለማካፈል፣ የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠትና በሚኒስቴሩ የተጀመሩ ስራዎችን በዲጂታል ስርዓት ለማዘመን ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት ድጋፍ እንደምታደርግ ገልፀዋል።

Please follow and like us: