የአፍሪካ ወጣት መሪዎች ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ የመክፈቻ ስነሥርዓት ተካሄደ

የአፍሪካ ወጣት መሪዎች ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ (AYLDC) የመክፈቻ ስነሥርዓት በስካይ ላይት ሆቴል ተካሄደ።

ኮንፈረንሱ የተዘጋጀው የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማህበር (EYDPA) እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ነው።

በኮንፈረንሱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ የምንመኛትን የበለፀገችና አንድነቷ የተረጋገጠ አፍሪካ እውን ለማድረግ ወጣቶች እምቅ አቅማቸውን ሊጠቀሙና በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል። በተለይም በአመራርነት ላይ ያሉ ወጣቶችን በማበረታታትና ሁሉን አቀፍ ተሳትፏኣቸውን በማረጋገጥ አህጉሪቷን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ይገባል ብለዋል።

የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ሐይለማሪያም ደሳለኝን በበኩላቸው ያለሰላም ጠንካሪ ኢኮኖሚን መገንባት፣ ፈጠራንና ዘላቂ ዕድገትን ማረጋገጥ አዳጋች መሆኑን ገልፀው ወጣቶች ችግሮችን በውይይት የመፍታት ልምድ ሊያዳብሩ እና በሰላም ግንባታ ሂደት ወሳኝ ሚናቸውን ሊጫወቱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የፓንአፍሪካኒዝም እሳቤ አቀንቃኙ ፕሮፌሰር ፓትሪስ ሉሙቧ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የነገዋ አፍሪካ እድል ፈንታ የሚወሰነው አሁን ላይ ባሉ ወጣቶች እንደሆነ ጠቁመዋል።

በመሆኑም የወደፊት የለውጥ መሪዎች እና ወኪሎች የሆኑት የአፍሪካ ወጣቶች በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ በጋራ የበለፀገች አፍሪካን ለመገንባት በትጋት ሊሰሩ እንደሚገባ አጽዕኖት ሰጥተዋል።

ኮንፈረንሱ ስለአመራርነት፣ ስለዲፕሎማሲ እና ስለ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት፣ ስለፈጠራ ሰፊ ውይይት ለማካሄድ ያለመ እንደሆነ የኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማህበር ዳይሬክተር ወጣት ኢንጂነር ጫላ አሰፋ ገልጿል። ኮንፈረንሱ የአፍሪካ ወጣቶች ድምጽ፣ አመለካከት እና ፍላጎት በሰፊው የሚደመጥበትና የሚንጸባረቅበትን ዕድል ይፈጥራል ብሏል።

ወጣት መሪዎች ከዲፕሎማቶችና ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠርና ተሞክሮ ለመለዋወጥ መድረኩ የበኩሉን እገዛ ያደርጋልም ብለዋል። ኮንፈረንሱ ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በመድረኩ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት፣ ዩኒቨርስቲዎችና ከሲቪክ ማህበራት የተውጣጡ ከ300 በላይ ወጣት መሪዎች እየተሳተፉ ይገኛል። በዕለቱ ወጣቶችን ለማብቃት እና በሌሎችም መስኮች የላቀ ስራ ለሰሩ አካላት እወቅና ተሰጥቷል።

Please follow and like us: