ሚኒስቴሩ በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ተጎጂ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የሰብዓዊ ድጋፍ አደረገ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኦሮሚያና በአፋር ክልሎች በፈንታሌ ወረዳ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ተጎጂ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች 12.5 ሚሊየን ብር የሚገመት የሰብዓዊ ድጋፍ አደረገ።

በድጋፍ ርክክቡ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ በዜጎች ላይ እጅግ የከፋ የማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ችግሮች እንዳይከሰቱ ለማስቻል የድጋፍ አገልግሎት ለሚሰጡ ባለሙያዎች ስልጠናዎች መሠጠታቸውን አስታውሰዋል።በዛሬው ዕለትም በስፍራው በመገኘት ከዚህ በፊት ቃል በገባው መሠረት ሀብት በማሰባሰብ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የምግብ እህልን ጨምሮ የህፃናትና የአዋቂ የአልባሳት ድጋፍ እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስና አልሚ ምግቦችን አበርክቷል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቀደም ሲል ከሌሎች ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመተባበር በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀዋል።በቀጣይም ዜጎች ወደቀደሞ ኑሮኣቸው ተመልሰው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማስቻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ሚኒስትሯ ተናግረዋል። የሁለቱ ክልሎች የስራ ሃላፊዎች በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለተጎጂ ወገኖች ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል። በዕለቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎቹ የተፈናቀሉ ወገኖችን ተዟዙረው በመጎብኝ አፅናንተዋል።

 

Please follow and like us: