Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የአፍሪካ ወጣቶች ፌስቲቫልን በጋራ ለማካሄድ የሚያስችል ውይይት ተካሄደ
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና ክብርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሙና አህመድ ከተባበሩት መንግስታት ረዳት ሴክሬተሪ ጀነራል እና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ዶ/ር ራሚዝ አልካባሮቭ ጋር የአፍሪካ ወጣቶች ፌስቲቫልን በጋራ ለማካሄድ የሚያስችል ውይይት አካሄደዋል።

በውይይቱ ወቅት የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ወጣቶች የበለጸገች እና ሰላም የሰፈነባት አፍሪካን በጋራ ለመገንባት የበኩላቸውን አስተዋፀዖ እንዲያበረክቱ ለማነሳሳትና ፓን አፍሪካኒዝምን ለማጠናከር እንዲያስችል የአፍሪካ ወጣቶች ፌስቲቫል በቅርቡ ለማካሄድ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ገልፀዋል። ፌስቲቫሉ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አዘጋጅነት ከተመድ፣ ከአፍሪካ ህብረት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በልዩ ልዩ መርሐግብሮች ለማካሄድ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ውይይቱ በዋነኝነት ፌስቲቫሉን በተሳካ መልኩ ማካሄድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ያለመ እንደሆነም ጠቁመዋል። ለአጀንዳ 2063 ስኬትም ሆነ የምንመኛትን አፍሪካ እውን በማድረግ ረገድ የወጣቶችን አይተኬ ሚና ለማጎልበትና የፓን አፍሪካኒዝምን እንቅስቃሴ ለማጠናከር ተመድና የአፍሪካ ህብረት እያደረጉት ላለው ድጋፍና ትብብር ክብርት ሚኒስትሯ ምስጋና አቅርበዋል።
