Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የረመዳንና የአብይ ፆምን በማስመልከት ማዕድ አጋራ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በተገኘው ድጋፍ በልደታ ክ/ከተማ ለሚገኙ ለማህበራዊ ችግር ተጋላጭ ወገኖች የረመዳን ፆምንና የአብይ ፆምን አስመልክቶ ለ 500 ሰዎች የዘይት ፣ድቄት፣ ሩዝና ቴምር የማዕድ ማጋራት አከናውኗል።

የሚኒስቴሩ ማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ሁሪያ አሊ እንደገለፁት መደጋገፍ ከሀይማኖት ባሻገር ደግነት እና ልግስና ሰው የመሆናችን ማሳያ የማህበረሰባዊ ግዴታ መሆኑን ጠቅሰዋል። መንግስት ከለውጡ ማግስት ዜጋ ተኮር ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደ ማዕድ ማጋራት አይነት ስራዎች ባህል እስኪሆን በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ማዕድ ማጋራቱ በዋናነት እርስ በርስ ስንተጋገዝ የማናልፈው ችግር አለመኖሩን ለማሳየትና ወገን እንዳላችሁና ሁሌም ከጎናችሁ መሆናችንን ለማሳየት ነው ሲሉ ተናግረዋል። የተቸገሩትን መደገፍ እና አለሁ ማለት በሁሉም ሃይማኖት ዘንድ የተቀደሰ ተግባርና የኢትዮጵያዊነት ባህል መሆኑን ገልፀው ዜጎች ከማህበራዊ ችግርና ከተረጂነት ተላቀው አምራች ሆነው ከራሳቸው አልፎም ለአገር እድገትና ብልፅግና አስተዋፅኦ እስኪያበረክቱ ድረስ መንግስት ዜጋ ተኮር ስራዎቹን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
Please follow and like us:
