የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የዜጎችን ህይወት በዘላቂነት መቀየርን መሠረት ላደረጉ ኘሮጀክቶች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተገለፀ።

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር የሆኑትን ሱነ ክሮግስረፕ ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት እንደገለፁት ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከውይይት በዘለል የዜጎችን ህይወት በዘላቂነት መቀየርን መሠረት ላደረጉ ኘሮጀክቶች ቅድሚያ እንደሚሰጥ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በተለይም ሴቶችንና የወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ኘሮጀክቶች የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው እንደሆኑ ገልፀው በተለይም በገጠራማው የሀገራችን ክፍል የሚገኙ ሴቶች ላይ ትኩረት በመስጠት አንዲሠራ ጠይቀዋል። ሴቶችና ወጣቶች በሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማሣደግ ሌላው ትኩረት የሚሻ የትብብር መስክ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ ያላት የሴቶችና ወጣቶች ምጣኔም ለሀገረ መንግስት ግንባታው ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብሎ መንግስት እንደሚያምን ጠቅሰዋል።

በውይይቱ የማህበራዊ ጥበቃ፣ የቤተሰብ ጉዳዮች እንዲሁም ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች መከላከልና ምላሽ መስጠት ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶች ላይ የዴንማርክ መንግስትና ሚኒስተር መስሪያቤቱ በቅንጅት መስራት እንደሚችሉ ሚኒስትሯ ገልፀዋል ። አምባሳደር ሱነ ክሮግስረፕ በበኩላቸው መንግስታቸው ከፈረንጆቹ 2025_2029 በኢትዮጵያ ለሚተገብራቸው ፕሮጀክቶችና በተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት በኩል በገንዘብ ለሚደግፋቸው ተግባራት ውይይቱ አዳዲስ የትኩረት መስኮችን ያመላከተና ለድጋፍ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

 

Please follow and like us: