ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት የ5 መቶ ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ እና 4ሺህ ኪሎ ግራም የቴምር ስጦታ አበርከተ

የፌዴራል ከፍተኛ ሴት አመራሮች የረመዳን ጾምን ምክንያት በማድረግ በባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት በመገኘት የኢፍጠር መርሐግብር አካሄዱ።

ሚኒስቴሩ ለበጎ አድራጎት ድርጅቱ የ5 መቶ ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ እና 4ሺህ ኪሎ ግራም የቴምር ስጦታ አበርክቷል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ ክቡራት ሚኒስትር ዴኤታዎችና እና ሌሎች የፌዴራል ከፍተኛ ሴት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል። የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፥ መንግስት እያከናወናቸው ካሉ ሰው ተኮር ተግባራት መካከል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙና አቅመ ደካማ ወገኖች በየጊዜው የሚያካሂደው ማዕድ የማጋራትና ሰብዓዊ ድጋፍ በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችንና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አቅመ ደካማ ወገኖችን ለመደገፍና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማስቻል በርካታ ስራዎችን በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በቀጣይም ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር መሠል ድጋፎችን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። እንደባቡል ኸይር ያሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በርካታ ዜጎችን በተለያየ መንገድ በመደገፍ የመንግስትን ጫና እያቃለሉና የሚደነቅ ስራም እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል። ህብረተሰቡ፣ ባለሃብቱና ባለድርሻ አካላት አቅም በፈቀደ መጠን እጅ አጠር የሆኑ ወገኖችን ለመደገፍ የተቋቋሙ የበጎ አድራጎት ተቋማትን በመደገፍ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ አናን መሐመድ በበኩላቸው፥ የሚመለከተን፣ የሚደግፈንና አለኝታ የሚሆነን ወገን ከጎናችን እንዳለ ማየት ችለናል ብለዋል። አመራሩ ትኩረት ሰጥተው ከወገኖቻቸው ጋር ኢፍጠርን ለማሳለፍ በመገኘታቸው መደሰታቸውን ገልፀው፥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል። በጎ አድራጎት ድርጅቱ ከ5ሺህ በላይ አባወራዎችን እየረዳና ሰፊ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ድጋፉ ወደፊትም ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል።

Please follow and like us: