Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የዘንድሮ በዓለም አቀፍ ቤተሰብ ቀንን አስመልክቶ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
በዓለም ለ32ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ3ኛ ጊዜ ‹‹የተሻሻለ የቤተሰብ ሥራና ገቢ ለሃገር ኢኮኖሚ›› በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ገልፀዋል።

ቤተሰብ የራሱን ደህንነት እና ጤንነት በመጠበቅ፣ ህጻናትን በመልካም ስብእና በመቅረጽ፣ አረጋውያንን እና አካል ጉዳተኞችን በመንከባከብ እና በማሳተፍ፣ ወጣቶች ለቀጣይ የቤተሰብ ምስረታ ተገቢውን ልምድ እና እውቀቶችን እንዲያገኙ በማድረግ፣ በቤት ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጥቃቶችን እና ጉዳቶችን በመከላከል፣ የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮችን ከቤት ውስጥ ጀምሮ በማረጋገጥ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ ንፅህና እና እንክብካቤ ጉዳዮች በቀጥታ በመሳተፍ፣ የህብረተሰቡን ትስስር በማጠናከርና ሰላምን እና ደህንነትን በማረጋገጥ፣ መልካም ጉርብትናን በማስፈን እና ማህበረሰባዊ ትስስርን በማጠናከር የህብረተሰብ መሰረትነቱን የሚያረጋግጥ ወሳኝ ተፈጥሯዊ ተቋም መሆኑን ጠቅሰዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቤተሰብ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ሚና ለማሳደግ ትኩረሸት ሰጥቶ ይሰራል፡፡ ድርጅቱ በጠቅላላ ጉባኤው ዲሴምበር 9/1989 ባደረገው ስብሰባ በውሳኔ ቁጥር (Resolution 44/82) እ.ኤ.አ 1994 የቤተሰብ አመት በሚል እንዲሰየም ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የቤተሰብ ቀን በየዓመቱ በዓለም-ዓቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ ግንቦት 15 ላይ ይከበራል፡፡ ከላይ እንደተገለፀው ቤተሰብ የህብረተሰብ የተፈጥሮ መሰረታዊ መነሻ እንደመሆኑ መጠን መልካም ስብዕና ያለውን ዜጋ በማፍራት እና የህብረተሰቡንም ትስስር ይበልጥ በማጠናከር ረገድ ቀዳሚ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል ።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገመንግስት አንቀጽ 34/3 መሰረት ቤተሰብ በመንግስት እና በህብረተሰቡ ጥበቃ የማግኘት መብት እንዳለው ተደንግጓል፡፡ እንዲሁም የአስፈፃሚ አካላትን ተግባርና ኃላፊነት ለመወሰን ባወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 የቤተሰብ ሁለንተናዊ ሚና ጎልቶ እንዲወጣ ‹‹ቤተሰብ እንደ ኅብረተሰብ ዋና መሠረት የተሰጠውን ሕገ-መንግሥታዊ ጥበቃ በተግባር ለማዋል የሚያስፈልጉ ስልቶችን ከሚመለከታቸው ክልላዊ መንግሥት አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ይነድፋል፤ተግባራዊነቱን ይከታተላል›› በሚል ለሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊነት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
