Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ሚኒስቴር መስሪያቤቱ የወጣቶች ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ አፈጻጸም ላይ ያሉ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታትና ያለበትን ደረጃ ለመገምገም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
በዕለቱ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ እንደገለፁት የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ የስራ ስምሪት አነስተኛ ካፒታል የሚጠቀምና ሰፊ የሰው ሃይል የሚያሳትፍ በመሆኑ ጠቀሜታው እጅግ የላቀ እንደሆነ ገልፀዋል።

መንግስት የወጣቶችን ችግር በሚፈለገዉ ደረጃ መፍታት የሚቻለዉ ለወጣቶች ምቹ የብድር ስርዓት በመፍጠር እና ወጣቶችን ፍትሃዊ የሀብት ተጠቃሚ በማድረግም ሆነ በህብረተሰቡ ዘንድ አስፈላጊ የሆኑ ምርትና አገልግሎቶችን በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው እንደሚያምን ጠቅሰው ለዚህም ወጣቶች የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ማጠናከርና ተደራሽነቱን በማስፋት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል ። የተዘዋዋሪ ፈንዱ ያስፈለገበት ምክንያትም የልማት ግቦቻችንን ስኬት በሀገራችን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የወጣቶችን ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ፤ የአበዳሪ ተቋማት ሚና ከፍተኛ ቢሆንም እነዚህ አበዳሪ ተቋማት ለወጣቱ ብድር ለማበደር ያላቸው መስፈርት ከፍተኛ መሆናቸውና የወጣቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑና ምቹ የሆና የብድር ስርዓት አለመኖር መሆኑ በዋናነት ተጠቅሷል።

አላማውም ወጣቶች ተደራጅተው ለሚያካሂዷቸው ገቢ ማስገኛ እንቅስቃሴዎች የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት፤ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሆኑን አስታውቀዋል ። በዚህም በርካታ ወጣቶች ተጠቃሚ መሆናቸው ቢታወቅም የተዘረጋው አሰራር ተግባራዊ ሲሆን በተፈጠረው ክፍተት አማካኝነት በተለይ ከመንቀሳቀሻ ካፒታል፣ ከአመለካከት፣ ከክህሎት ከቅንጅታዊ አሰራር፤ የብድር አመላለስ ግንዛቤ እጥረት፣ ከመስሪያ ቦታ ጋር በተያያዘ ክፍተቶች እንዳሉ በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ ግምገማዎች መገንዘብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በመድረኩ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ድኤታ አቶ ሰለሞን ሳንካ በበኩላቸው ወጣቶች ያላቸውን አቅም ለስራ እድል ፈጠራ እንዲያውሉ እገዛ ለማድረግ ቢሆንም በአፈፃፀም ወቅት ተግዳሮቶች እንደነበሩበት ገልፀው ሚኒስቴር መስሪያቤታቸውም አዲስ ረቂቅ አዋጅ እያዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰዋል። እንደ መፍትሔ ከተቀመጡ አቅጣጫዎች መካከልም የቅንጅት ስራዎችን ማጠናክር ፣የወጣቶች የስራ ተነሳሽነት የስራ ባህልን የብድር አመላለስ ግንዛቤ ማሳደግ እና አዳዲስ የስራ ፈጠራ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ማስቻል እንዲሁም የተጠያቂነት ስርአት መዘርጋት እና በየደረጃው ተቋቁሞ የነበረው ግብረ ኃይል ተግባርና ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግ ቢቻል በቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም ማግኘት እንደሚቻል በመድረከ ተነስቷል። ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ለወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ የሚውል 10 ቢሊዮን ብር የተዘዋዋሪ ፈንድ መመደቡ ይታወሳል።
