ወጣቱ ትውልድ ከእድሜ ባለፀጎችና ከታላላቆች እውቀትና ልምድን በመቅሰም ለማህበረሰብ ለውጥ ብሎም ለዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ እድገት የድርሻውን መወጣት አለበት – ክቡር አቶ ጌታቸው በዳኔ

የትውልድ ቅብብሎሽ መድረክ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በተለያዩ መርሐግብር ተካሂዷል።

በመድረኩ በሚኒስቴር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስትር አማካሪ ክቡር አቶ ጌታቸው በዳኔ አረጋዊያን ለወጣቱ ትውልድ ታሪክን፣ ባህልን፣ ስነ-ምግባርን፣ ስራ ወዳድነትንና የአመራርነት ጥበብን በዘዴ የማስተማር ብሎም ለተሳካ የትውልድ ቅብብሎሽ ድልድይ ሆነው እያገለገሉ መሆናቸውን ገልፀዋል። ወጣቱ ትውልድ ተንቀሳቃሽ ቤተ-መፅሐፍት ከሆኑት አረጋውያንና ታላላቆች ልምድንና ጥበብን በመቅስም ለራሱም ሆነ ለቤተሰቡ እንዲሁም ለማህበረሰብ ሁለንተናዊ ለውጥ ብሎም ለዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ እድገት የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የረጅም እድሜ፣ እውቀትና ልምድ ባለፀጋ ለሆኑት አረጋውያን መብት መከበር፣ ማህበራዊ ደህንነት መጠበቅ፣ ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት መረጋገጥ እንዲሁም ለመልካም እሴት ግንባታ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ የማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ረዳት ፕሮፌሰር ገነነ ገደቡ መልካም ዜጋ ለማፍራትና የተሳካ የትውልድ ቅብብሎሽ ስርዓት እንዲኖር ዘርፉን ያማከሉ የአሰራር ማዕቀፎች እንዲወጡና ተፈፃሚ እንዲሆኑ ምክር ቤቱ የተጠናከረ የክትትልና ድጋፍ ስራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በሚኒስቴሩ የአረጋውያንና ቤተሰብ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋዬ ሮበሌ በበኩላቸው የመድረኩ ዓላማ የአረጋውያንና የታላላቆችን እውቀትና ልምድ ለወጣቱ ትውልድ ማሸጋገር የሚያስችል መደላድል ለመፍጠር ብሎም ተገቢውን ክብር፣ ፍቅርና እንክብካቤ መስጠት እንደሚገባ ለወጣቱ ለማስገንዘብ እንደሆነ ተናግረዋል። “የትውልድ ቅብብሎሽ፤ ባለፈው፣ በዛሬና በነገይቱ ኢትዮጵያ ባሉ እድሎች፣ ፈተናዎችና መፍትሔዎች ላይ አነቃቂ መልዕክቶችን ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ዶ/ር ጃራ ሰማ “አዎንታዊ አስተሳሰብ ካለፈው ተምረን ዛሬን አፅንተን ወደ ነገ ለመሻገር የሚያስችል ለተሳካ የትውልድ ቅብብሎሽም ሆነ ለሀገር ግንባታ ወሳኝ መሆኑን” አንስተዋል።

የሀገር ባለቤትና ተስፋ የሆነው ወጣቱ ትውልድም ብልህና የበጎ አመለካከት ባለቤት እንዲሆን እንዲሁም ፅናትና ትዕግስትን በመላበስ፣ እርስ በእርስ በመደጋገፍና በትጋት በመስራት ራሱንም ሀገሩንም መለወጥ እንዳለበት፤ ለዚህም ከቤተሰብ ጀምሮ በትኩረት መሠራት እንደሚገባ በአፅዕኖት አስገንዝበዋል። በመድረኩ መምህርትና ተመራማሪ ፕ/ር ያለምፀሀይ መኮንን፣ የእድሜ ባለፀጋው አቶ ፀጋ መለሰ እና ኮማንደር መስከረም ብሩ ለትውልዱ ትምህርት ሰጪ ተሞክሮና የህይወት ልምዳቸውን አካፍለዋል።

Please follow and like us: