የሲዳማ ክልል የወጣቶች ምክር ቤት ተመሰረተ

በመድረኩ የክልሉ የፕሬዝደንት አማካሪ አቶ አሸናፊ ኤሊያስ በንግግራቸው እንደገለፁ፤በምክንያታዊነትና በሀሳብ የሚያምን የሀገርን ብሔራዊ ጥቅሞች የሚያስጠብቅ ወጣት ለማነፅ በጋራ መስራት አለብን ብለዋል ።

በተጨማሪም ወጣቱን በኢኮኖሚ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚገባም ገልፀዋል። በምስረታ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በመወከል ወ/ሮ የሺወርቅ አያኔ እንዳሉት ወጣቶች ካላቸው እምቅ አቅም፣ እውቀትና ክህሎት አንፃር ራሳቸውን ከመለወጥ ባለፈ ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ መንግስት የወጣቶችን ችግሮች ለመፍታት፣ መብታቸውንና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እመቤት ኢሳያስ በበኩላቸው ወጣቶች ለሀገራዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እያደረጉት ያለው ንቁ ተሳትፎ እየተሻሻለ መምጣቱንና የወጣቱን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተለያዩ አደረጃጀቶች በማካተት ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ እየተደረገ እንደሚገኝም አክለው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ፕሬዚዳንት ወጣት ፉዓድ ገና የወጣቶች ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ በመሆኑ በወጣቱ ላይ ሊኖረን የሚገባው ግብ ወጣቱ ራሱንም አብቅቶ በማህበረሰቡና በአካባቢው የልማት፥ሰላምና ዲሞክራሲ ቀንዲል ከመሆን አልፎ ሀገራችን ለጀመረችው የብልፅግና ጉዞ መሪና ተዋናይ በመሆን በምትመካከር ኢትዮጵያ ውስጥ የተግባባ ትውልድ በመፍጠር የተከበረችና የበለፀገች ሀገር መስራት ይጠበቅብናልም ብለዋል።

በተጨማሪም የክልሉ ወጣቶች ምክር ቤት ሰብሳቢ የሆኑት ወጣት ይስሀቅ ሳንቡሬ በበኩላቸው ወጣቶች የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረትም የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባም ገልፀው ወጣትነት አካላዊና ስነ-ልቦናዊነት ፀጋን የታደለ ስለሆነ ያለንን አቅም ለሀገር ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ዕድገት ልናውል ይገባልም በማለት መልዕክትም አስተላልፈዋል። በመጨረሻም ዛሬ በተደረገው የወጣቶች የምክር ቤት አባላት የምስረታ መርሃ-ግብር ላይ አባላት የቃለ-መሃላ ስነ-ስርዓት በመፈፀም አጠናቀዋል ። በመድረኩ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚዎች፥ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

Please follow and like us: