Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የዩኤን ውመን/UNWOMEN/ ተወካይ ሃላፊ ማዳም ዶሪ ሞፕኡሞኡን ተቀብለው አነጋገሩ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የዩኤን ውመን/UNWOMEN/ ልዩ ተወካይ እንዲሁም በኢትዮጵያ የዩኤን ውመን/UNWOMEN/ ተወካይ ሃላፊ ማዳም ዶሪ ሞፕኡሞኡን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሁለቱ የስራ ሃላፊዎች የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ከማረጋገጥና ሴቶችን ከማብቃት አኳያ በተከናወኑ ተግባራትንና በሂደት ላይ ባሉ ኢኒሼቲቮችን ዙሪያ በሰፊው ተወያይተዋል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ክብርት ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ጊዜ፤ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለማስቆም እንዲሁም የሴቶችን አቅም በክህሎት ለማበልፀግና ወደ አመራርነት እንዲመጡ ለማስቻል ውጤታማ ስራ መሠራቱን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ ሴቶች የሰላምና ደህንነት ብሔራዊ የድርጊት መርሐግብር እና ብሔራዊ የስርዓተ ፆታ እኩልነትና ሴቶችን የማብቃት ፖሊሲ ዝግጅት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ብዙሃን ሴቶች በገጠር የሚኖሩ እንደመሆኑም በተለይ በግብርናው መስክ በስፋት እንዲሰማሩና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ ፕሮግራም ለመተግበር እቅድ መነደፉን አስረድተዋል።የስርዓተ ፆታ ጉዳይ አካቶ ትግበራና ውጤታማነትን ለማረጋገጥና ተጠያቂነትን ለማስፈን በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል። በሚኒስቴሩ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ስኬታማ እንዲሆኑ ዩኤን ውመን/UNWOMEN/ እያደረገ ላለው ጠንካራ ድጋፍ ክብርት ሚኒስትሯ ምስጋና አቅርበው በቀጣይም በሂደት ላይ ያሉትንና አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን ወደ ስራ ለማስገባት ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የዩኤን ውመን/UNWOMEN/ ልዩ ተወካይ እንዲሁም በኢትዮጵያ የዩኤን ውመን ተወካይ ሃላፊ ማዳም ዶሪ ሞፕኡሞኡ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት የስርዓተ ፆታ እኩልነትንና ሴቶችን ለማብቃት እየወሰደ ባለው ጠንካራ እርምጃ የመጡ ውጤቶችን አድንቀዋል። ዩኤን ውመን በዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጡ በጋራ እንደሚሰራና ድጋፍም እንደሚያደርግ ማዳም ዶሪ ተናግረዋል።
