Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ሚኒስቴሩ ሴቶችን አካትችና የተሻለ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በቅንጅት ይሰራል – ክቡር አቶ ጌታቸው በዳኔ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዓለም ባንክ የሥርዓተ-ፆታ ፈጠራ ጋር በመተባበር ባካሄዱት የ2025 የባንኮች የስርዓተ ፆታ አካታችነት ምዘና መስፈርት መሰረት እናት ባንክ ለሴቶች የተለየ የባንክ አገልግሎት በማቅረብ የመጀመሪያ እና ብቸኛ ትራንስፎርሜሽናል ባንክ ሆኖ ተመርጧል፤ ይህንኑ ምክንያት በማድረግ በሂልተን ሆቴል ልዩ መርሐግብር ተዘጋጅቷል።

በመርሐግብሩ ላይ የእናት ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን ለሴቶች የተለየ የባንክ አገልግሎት ማቅረብ፣ በፈጠራ የተደገፈ የባንክ አሠራር መዘርጋት እንዲሁም ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንኮች ሁሉን አካታችነት የባንክ አገልግሎት መስፈርቶች መሆናቸውን አስገንዝበዋል። እናት ባንክም እነዚህን መስፈርቶች ሟሟላቱ፣ ከባንኩ ከ55 በመቶ በላይ አመራሮች ሴቶች መሆናቸው፣ ከ22ሺህ በላይ ለሆኑ ስራ ፈጣሪ ሴቶች 1.4 ቢሊየን ብር ካለ ዋስትና በማበደር የራሳቸውን ስራ እንዲጀምሩ መደረጉ ቀዳሚ እንዳስባለው ጠቁመዋል።

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክብርት ሚኒስትር አማካሪ ክቡር አቶ ጌታቸው በዳኔ በበኩላቸው የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃትና ተጠቃሚነታቸውን ለማድረግ በርካታ ተግባራት በቅንጅት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል። እናት ባንክ ወደፊትም ከዘመኑ ጋር የሚራመድ ዘመናዊ ቴክኖሎጂና አሠራር በመተግበር ሴቶችን ይበልጥ አካታችና ተደራሽ ያደረገ አገልግሎት ከመስጠትና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ከማጎልበት ባሻገር በዘርፉ የተጣለው ሀገራዊ ግብ እንዲሳካና በአለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ ለመሆን በላቀ ትጋት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።

ሚኒስቴሩ በቀጣይም እንደሀገር ሴቶችን አካትችና የተሻለ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የሚደርጉትን ጥረቶች እንደሚደግፍና ወደፊትም በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
