የአገልግሎት ክፍተቶችን ለመሙላት የአሰራር ባህልን ለመቀየርና ጠንካራ ተቋም ለመገንባት ሪፎርሙን በተሟላ መልኩ መተግበር ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ዘርፍ የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ሰነድ ላይ የውይይትና ግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ አካሂዷል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስራ አስፈፃሚ አቶ አሳልፈው አህመዲን ሰነዱን ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለውጡን ተከትሎ ሁሉን አቀፍ የመንግሥት አገልግሎትና አስተደደር ሪፎርም ተግባራዊ እያደረገችና ውጤትም እያስመዘገበች ትገኛለች። የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችን ለመሙላት፣ የአሰራር ባህልን ለመቀየርና ጠንካራ ተቋም ለመገንባት ሪፎርሙን በተሟላ መልኩ መተግበር ወሳኝ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በየዘርፉ የአገልጋይነት አመለካከት የተላበሰ ብሎም በእውቀትና ክህሎት ረገድ ብቃትን መሠረት ያደረገ አሰራር ከመገንባት ጎን ለጎን የሰው ኃይል አስተዳደር ስርዓቱን ማዘመን እንደሚገባም ተናግረዋል። ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግልጽና ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ዘመናዊ እንዲሁም ከብልሹ አሰራር የፀዳና ተጠያቂነት ያረጋገጠ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስርዓትን ለመገንባት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ለስኬታማ የሪፎርም ትግበራም ተናቦና ተባብሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ሃላፊው አፅዕኖት ሰጥተዋል። በቀረበው የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያ ሰነድ ዙሪያ በተሳታፊዎች ግብዓት የተሰጠ ሲሆን ማብራሪያ በሚሹና ተያያዥ ጉዳዮች ላይም ምላሽና የቀጣይ አቅጣጫ ተቀሞጧል።

 

Please follow and like us: