Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ባለፉት የለውጥ አመታት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸው ተገለፀ
ባለፉት የለወጥ አመታት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለፁ።

ክብርት ሚኒስትሯ እንደተናገሩት፤ በፖለቲካው መስክ የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት አቅም ለማሳደግ ሰፊ ስራ መሰራቱንም አክለው ገልፀዋል። በዚህም በእንደራሴዎች ምክር ቤት የሴቶች ድርሻ 41%፣ በሚኒስትር ደረጃ 50.3% እንዲሁም በሚኒስትር ዴኤታ ቦታዎች 29% መድረሱን ገልፀዋል። በዚህ ረገድ ለተገኘው ውጤት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ትልቁን ድርሻ ተወጥተዋል ብለዋል። በኢኮኖሚው ረገድም ባለፉት 5 አመታት ከ12 ሚሊዮን በላይ ሴቶች በህብረት ስራ ማህበራት በአባልነት መታቀፋቸውን፣ 50 ሚሊዮን 303 ሺህ 217 ሴቶች በቁጠባ መሳተፋቸውን እና ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ መቆጠብ መቻላቸውን አስታውቀዋል። የሴቶች የብድር አገልግሎት ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንና በተለያዩ መስኮች በመሰማራት የኢኮኖሚ አቅማቸውን ማጎልበት እንዲችሉም ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ክብርት ሚኒስትሯ ተናግረዋል። በሌላ በኩል የከተማና የገጠር ሴቶች የንብረት ባለቤትነት መብት እንዲረጋገጥ መደረጉንና ይህም ሴቶች ከጥገኝነት ተላቀው የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ እያደገ መምጣቱ እንዲሁም በጤና ተቋም የሚወልዱ ሴቶች ቁጥር መጨመሩ በማህበራዊ ዘርፍ ከተገኙ አበረታች ውጤቶች መካከል በጉልህ የሚጠቀሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል። የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቆም ጠንካራ ስራ መሠራቱንና በተዘጋጀው መስፈርት መሠረትም 1 ሺህ 165 ቀበሌዎች ነፃ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። ድርጊቱን ለመከላከል ሀገራችን ኢትዮጵያ በወሰደችው ጠንካራ እርምጃና በቅንጅት በተሰራው ስራ አለም አቀፍ እውቅና ማግኘቷን አስታውሰዋል።
