Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮ – ሞሮኮ የአብሮነትና የኢኮኖሚ ትብብር ሳምንት በአዲስ አበባ ተጀምሯል
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሞሮኮ ኤምባሲ ጋር በመተባበር የተዘጋጀውና በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች የምርት ውጤት ማሳያ ኤግዚቢሽን በዛሬው ዕለት በስካይላይት ሆቴል እየተካሄደ ይገኛል።
ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ጊዜ፥ ኢትዮጵያና ሞሮኮ ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ባሻገር ሰፊ ታሪካዊና ባህላዊ ትውፊት ያላቸው ጥንታዊ ሀገራት መሆናቸውን አንስተዋል። የኢፌዴሪ መንግስት ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃትና የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። በመላ ሀገሪቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ ሴቶች በህብረት ስራ ማህበራት ተደራጅተው ራሳቸውን ከመጥቀም ባለፈ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረክቱ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ከ26 ቢሊዮን በላይ ብር መቆጠብ መቻላቸውንም አክለው ገልፀዋል።
የለውጥ አስኳል የሆኑት ሴቶች በኢኮኖሚ እንዲበቁና የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ በቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስ፣ በመሠረተ ልማትና በስልጠና መደገፍ ይገባል ብለዋል።
እንደአህጉር አካታች፣ ዘላቂና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመፍጠር በትብብር መስራት ያስፈልጋል፤ መሠል የልምድ ልውውጥ ተግባራትም ወደፊት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
የሞሮኮ አምባሳደር ማዳም ነዚሃ አሎይ መሃመዲን በበኩላቸው፥ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው አጋርነት መጠናከር አስደሳች መሆኑን አስታውሰው በዚህ ኢግዚቢሽን ስምንት የሞሮኮ ሴቶች የህብረት ስራ ማህበራት እና ሁለት ስታርት አፕ ፕሮግራሞች እንደሚሳተፉ እና ከኢትዮጵያ አጋሮቻቸው ጋር ጠቃሚ ልምድን እንደሚለዋወጡ ጠቅሰዋል። በመድረኩ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ሴት የህብረት ስራ ማህበራት አባላትና የሚዲያ አካላት ተገኝተዋል። ኤግዚቢሽኑ ለቀጣይ ሁለት ቀናት እንደሚቀጥል ተገልጿል።
