ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማዕከል አድርጋ እየሰራች ነው-ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማዕከል አድርጋ እየሰራች እንደምትገኝ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ተናገሩ።
‎
‎ሁለተኛው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
‎
‎የጉባኤው አካል የሆነ የውይይት መድረክ “ወጣቶች እንደ ለውጥ ፈጣሪ፥ ጥበብና ፈጠራ ለለውጥ እና ዘላቂ የምግብ ስርዓት ያላቸው ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።
‎
‎የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በውይይት መድረኩ ላይ እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የምግብ ዋስትናን እያረጋገጠች እንዲሁም ሰፊ የስራ ዕድል እየፈጠረች ነው።
‎
‎በሌማት ትሩፋት፣በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና ሌሎች የምግብ ዋስትናን በሚያረጋግጡ የምጣኔ ሃብት ዘርፎች ወጣቶችን በንቃት በማሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ብለዋል።
‎
‎በግብርናው ዘርፍ ለሚፈጠሩ የስራ ዕድሎች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ ለግብርና ቴክኖሎጂ እና ወጣቶች በምግብ ስርዓት ላይ ያላቸውን ሚና ማሳደግ በጉባኤው ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት።
‎
‎የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሃመድ በበኩላቸው፥ በዓለም የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የምግብ ስርዓት ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑን አንስተዋል።
‎
‎ለችግሮች መፍትሄ በመስጠት የተመድ የዘላቂ ልማት ግቦችና የአፍሪካ አጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
‎
‎ለወጣቶች ብልጽግና እና ስራ ፈጠራ ከፖሊሲ ጀምሮ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጨምረዋል።
‎
‎እንደ ምክትል ዋና ጸሐፊዋ ገለጻ፥ በዓለም የምግብ ስርዓት ቀጣይነት ያለው ለውጥ ለማምጣት ትብብርን ማጠናከር፣ትርክትን መቀየር፣ ለወጣቶች ስራ ፈጠራ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው።
‎
‎በውይይት መድረኩ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ተወካዮች፣ፖሊሲ አውጪዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች፣ወጣቶችና ሌሎች የተገኙ ሲሆን ወጣቶች ዘላቂ የምግብ ስርዓትን ለማረጋገጥ ያላቸው ቁልፍ ሚና በስፋት ምክክር ተደርጎበታል።
‎
‎በኢትዮጵያ፥ በጣልያን እና በተመድ ትብብር የተዘጋጀው ሁለተኛው የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ዋና ዓላማው የዓለም የምግብ ሥርዓትን ማሻሻል ነው ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Please follow and like us: