Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው የአለም የስርዓተ ምግብ ጉባኤ ጎን ለጎን በአፍሪካ ውስጥ በግብርና ስራ ላይ የተሰማሩና በገጠር የሚኖሩ ሴት የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚያበረታታና የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር የሚደግፍ ‘አንድ ችግኝ ለአንድ ሴት’ የተሰኘ አፍሪካዊ ኢኒሼቲቭ ተጀመረ።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ኢንሼቲቭ በመላ አገሪቱ ሴቶችን ጨምሮ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች አሳታፊና አካታች ባደረገ መልኩ እየተገበረች ትገኛለች ብለዋል።

ባለፉት 6 ዓመታት ከ 43 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመከተል የተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ትልቅ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል። ከኢትዮጵያ ተሞክሮ በመማር የሚጀመረው በአፍሪካ ደረጃ ’አንድ ችግኝ ለአንድ ሴት’ ኢኒሼቲቭም ዘላቂ ልማትንና የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና ሴቶችንም በኢኮኖሚ ለማብቃት የሚደረገው ጥረት ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣ አጋዥ መሆኑን ገልፀዋል። በተለይ የገጠር ሴቶች ለግብርናው ዘርፍም ሆነ ለማህበረሰቡ ዕድገት የጀርባ አጥንትና የለውጥ ወኪል መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሴቶች በዘርፉ የሚገጥማቸው ችግር እንዲፈታ፣ ጥረታቸው ተገቢው እውቅና እንዲያገኝና የድካማቸውን ያህልም ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ አካታች ፖሊሲ በመቅረፅና በመተግበር፣ ኢንቨስትመንትን በማሳደግና አጋርነትን በማጠናከር ባለድርሻ አካላት ቁርጠኛ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል። የጊኒ የፕላንና አለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ክቡር ኢስማኤል ናቤ በበኩላቸው፥ በግብርናው ዘርፍ ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃት የመሬት ባለቤትነት መብት የበለጠ እንዲረጋገጥ፣ የብድር አቅርቦት፣ የስልጠናና የምክር አገልግሎት በስፋት እንዲመቻች በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
መድረኩን የአፍሪካ ሴት መሪዎች ጥምረት/AWLN/ ከዪ ኤን ውመን /UNWOMEN/ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን በመርሃ-ግብሩ ላይ የአፍሪካ ሴት መሪዎች ጥምረት አባል ሀገራት ተጠሪዎች፣ የአፍሪካ ህብረትና የአለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እና ሴት አርሶ አደሮች ተገኝተዋል።
