ኢትዮጵያ እና ኳታር በስትራቴጂካዊ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማሙ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የኳታር አምባሳደር የሆኑትን ሳድ ቢን ሙባረክን በፅ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱ ወቅት ሚኒስትሯ እንደገለፁት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለፉት የለውጥ አመታት በሴቶች፣ህፃናት ወጣቶች፣አካል ጉዳተኞች እንዲሁም ለችግር ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍና ለማብቃት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው ከኳትር መንግስት ጋርም ቀጣይ በስትራቴጂካዊ የትኩረት መስኮች ዙሪያ ለመስራት ማቀዳቸውንም ገልፀዋል።

በተለይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ትኩረት ከሰጣቸው ስራዎች መካከል በእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩ ሴቶችን ማጠናከር፣ ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የቤት ግንባታዎችን መገንባት፣ የወጣት የስብዕና ማዕከላትን መደገፍ፣ ለህፃናት መማሪያ የሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶችን ማስፋፋት እና የአረጋውያን ድጋፍና ክብካቤ ማዕከላትን ማቋቋም ላይ የኳታር መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል።

በኢትዮጵያ የኳታር አምባሳደር የሆኑት ሳድ ቢን ሙባረክ በበኩላቸው መንግስታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ጠንካራ ቁርጠኝነት እንዳለው ገልፀው በተለይም ከሚኒስቴሩ ስትራቴጂካዊ የትኩረት አቅጣጫዎች ጋር በተጣጣሙ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀረቡት መስኮች ላይ በጋራ ለመስራት ያመች ዘንድ በኳታር ልማት ድርጅት እና በሚመለከታቸው ተቋማት ጭምር ድጋፍ ለማሰባሰብ ያላቸውን ዝግጁነት ገልፀዋል ።

Please follow and like us: