Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
መንግስት የሴቶችን የአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ሚና የበለጠ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ።
መንግስት የሴቶችን የአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ሚና የበለጠ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አደም ፋራህ ገልፀዋል።

ክቡር አቶ አደም ፋራህ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፣ መንግስት የሴቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የፖለቲካ ተሳትፎ ካልተረጋገጠ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደማይቻል ያምናል ብለዋል። ባለፉት አመታት በታሪክ የወረስናቸውን ስብራቶች የሚጠግን የተዛቡ ትርክቶችን የሚያስወግድ የሴቶችን አቅም ወደ ተግባር የሚቀይር ስራ ተሰርቷል ብለዋል። በዚህም በፌደራልና በክልል ምክር ቤቶች እንዲሁም በርዕሰ መስተዳደር ደረጃ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና በሌሎች ከፍተኛ የአመራርዐቦታዎች ሴቶች ተሳታፊ መሆን እንደቻሉ ጠቁመዋል።

ይህም በኢትዮጵያ ሴቶች የውሳኔ ሰጪነት ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው ያሉ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በልማት ዕቅዶች ውስጥ የሴቶችን ጉዳይ በማካተት እየተሰራ ነው ብለዋል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሌማት ትሩፋት፣ በስራ ዕድል ፈጠራና፣ በሴቶች ላይ የነበሩ የተዛቡ አመለካከቶችን በመቀየር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸውን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሁሉንም ዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ሙሉ ዕይታ መፈጠሩንም ጠቅሰው፤ በዚህም የሴቶችን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲፈጠር መደረጉንም አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲጎለብት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ለተሰጠው ልዩ ዕውቅና ምስጋና አቅርበዋል።
