ወጣቶች በዲፕሎማሲና በዓለም አቀፍ ግንኙነት ዙሪያ ያላቸውን ክህሎት በማጎልበት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ መትጋት አለባቸው – ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ ገለፁ

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ለአንድ ወር በዲፕሎማሲና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዙሪያ ለወጣት ተማሪዎች በሰመር ካምፕ ሲሰጥ የነበረውን ሥልጠና አጠናቋል።

‎በስልጠናው ማጠቃለያ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ፥ የወደፊቷ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የለውጥ አስኳልና የልማቱ ዋነኛ መዘውር በሆኑት ወጣቶችዋ ትከሻ ላይ መሆኑን ገልፀዋል። ወጣቶች ያላቸውን እምቅ አቅም ለሀገር ሰላም፣ እድገትና ብልፅግና በማዋል አይተኬ ሚናቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፤ ለዚህ ደግሞ ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ብለዋል። ‎በዲፕሎማሲና በዓለም አቀፍ ግንኙነት ዙሪያም ዘመኑን የዋጀና ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ ክህሎት በመታጠቅና በየጊዜው ራሳቸውን በማብቃት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በትጋት መስራት እንዳለባቸው ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ አስገንዝበዋል። ዲፕሎማሲ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ በዘርፉ ብቁና ተተኪ ወጣቶችን ለማፍራት ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ተናግረዋል።

‎‎በዚህ ረገድ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በክረምት መርሐግብር በወጣቶች ላይ የጀመረው ተግባር አበረታች መሆኑን በመግለፅ ምስጋና አቅርበዋል። ኢንስቲትዩቱ በዲፕሎማሲና የዓለም አቀፍ ግንኙነት የወጣቶችን ክህሎት ለማዳበር እየሰጠ ያለውን ስልጠና አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልፀው፥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። ‎የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በበኩላቸው፤ ዲፕሎማሲ ሀገራችን የሰነቀችውን የብልፅግና ራዕይ ለማሳካት ቁልፍ ሚና ካላቸው ዘርፎች መካከል ግንባር ቀደም መሆኑን ገልፀዋል።

Please follow and like us: