Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ተመሣሣይ መረዳትና ተግባቦት መፍጠር የሕዝቦችን ሁለንተናዊ ፍላጎት ለማሳካት እንደሚረዳ ተገለፀ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮችና ሠራተኞች “ብሔራዊ ጥቅምና ጂኦስትራቴጅካዊ ቁመና” በሚል ርዕስ በሚኒስቴር መ/ቤቱ አዳራሽ ውይይት እያካሄዱ ነው።
በዕለቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለፁት፥ በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ተመሣሣይ መረዳትና ተግባቦት መፍጠር የሕዝቦችን ሁለንተናዊ ፍላጎት ለማሳካት እንደሚረዳ ገልፀዋል። ይህም ውስጣዊ ብሔራዊ አቅምን ማጠናከር እና በሁለንተናዊ መስኩ ራስን መቻል የጂኦስትራቴጂ ተፈላጊነት ፋይዳ መሠረት መሆናቸውን ጠቅሰው የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ላይ ውስጣዊ አንድነታችንን በማጠናከር በጋራ መቆም እንዳለብን ጠቁመዋል።
የመወያያ ሰነዱን ያቀረቡት የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ሁሪያ አሊ እንዳብራሩት፥ ብሔራዊ ጥቅም ምንድን ነው፣ እንዴት ይገለጻል፣ ጂኦስትራቴጅካዊ ቁመና ዕሳቤ ምንድን ነው? በሚለው ዙሪያ ሰፊ ገለፃ አድርገዋል። በዚህም ዜጎች አሁን ካለው ዓለም አቀፍ ግንኙነት አንጻር የአገራት ግብ፣ ፍላጎትንና ትኩረትን በአግባቡ መረዳት እንዲሁም የዓለም አገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚያስችላቸው ዕሳቤዎችን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።
በተጨማሪም የአገራት ሕልውና፣ ደህንነትና ዕድገት ይበልጥ ከጂኦስትራቴጅያዊ ቁመና ጋር የተቆራኘ መሆኑን በሚገባ ማወቅ ለሕዝቦች ጥቅምና ለአገር ዕድገት ብሎም ለቀጣዩ ትውልድ ምቹ መደላድል በመፍጠር አገራችንን ለማሻገር መሰረት ይጥላል ሲሉ አሰገንዝበዋል፡፡ ሀገራዊ ሕልውናን ማስቀጠልና ብሔራዊ ደኅንነትን ማረጋገጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናን ማሳካት፣ የዴሞክራሲ ሥርዐትን ማጎልበት፣ ፖለቲካዊ ዐቅምን ማዳበር እና ተፅዕኖ መፍጠር፣ የባህል ነፃነትን ማረጋገጥ እንዲሁም የሕዝቡን ማኅበራዊ ልማት ማረጋገጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ምሰሶዎች እንደኾኑም ሚኒስትር ድኤታዋ አስገንዝበዋል ።
የአገርን ጥቅምና የሕዝብን ፍላጎት ከሚጎዱ፣ ለባዕድ አገራት ምቹ አጋጣሚ፣ ብሔራዊ ጥቅምን የአገርን ደህንነት ወደ ኋላ ከሚያስቀሩ እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስከበርም የሕዝብን ፍላጎቶች ለማሳካት ከሚያሳንሱ ዕሳቤዎችም ሆነ አሰላለፎች መራቅና የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ ተገንዝቦ ለሀገራችን መትጋት የተገባ መሆኑንም ጨምረው አብራርተዋል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎች የቀረበው ሰነድ ወቅታዊ እና ጥልቀት ያለው ግንዛቤ የፈጠረ መሆኑን አንስተዋል። በገለፃው መሠረት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች እና ጂኦስትራቴጂያዊ ዐቅሞች ተገንዝበው የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱም ተናግረዋል፡፡
