Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ወጣቶችን በመስኖ እርሻ በማሰማራት ለአግሮ ኢንደስትሪ ፓርኮች የሚሆን ግብአት እንዲያቀርቡ ለማስቻል በመተግበር ላይ ያለው ፕሮጀክት አፈፃፀምና የቀጣይ እቅድ ተገመገመ
ወጣቶችን በመስኖ እርሻ በማሰማራት ለአግሮ ኢንደስትሪ ፓርኮች የሚሆን ግብአት እንዲያቀርቡ ለማስቻል በመተግበር ላይ ያለው (Production Enhancement Support to the Integrated Agro Industrial Parks & Youth Employment/PESAPYE) ፕሮጀክት የ2017 የስራ አፈጻጸም እና የ2018 እቅድ ተገምግሟል።
ፕሮጀክቱ በስትሪንግ ኮሚቴ የሚመራ ሲሆን ኮሚቴው ባካሄደው 2ኛው የግምገማ መድረክ ከፌዴራልና ከክልል የተውጣጡ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብርሃም በላይ በዚሁ ወቅት፥ ፕሮጀክቱ ያቀዳቸውን የመሰረተ ልማት፣ የወጣት ማህበራት ማደራጀት፣ የመሬት ዝግጅትና የፋይናንስ ድጋፍ ትግበራ ስራዎች በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ሊያጠናቅቅ እንደሚገባው አሳስበዋል። ለስራው መሳካትም ፕሮጀክቱ የሚተገበርባቸው የኦሮሚያ፣ የአማራና ሲዳማ ክልሎች የዘርፉ አመራሮች ከመሬት አስተዳደር፣ ከወጣቶች አደረጃጀት እና ከግንባታ ጋር ያሉ ችግሮችን ሊፈቱ ይገባል ብለዋል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፥ የመስኖ ልማቱ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ለወጣቶች ስራ እድል በመፍጠር የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል። ወጣቶቹ ዘመናዊ እርሻ የሚያከናውኑበት የማሽነሪ አቅርቦት ከወዲሁ አብሮ ሊሰራበት እንደሚገባም ክብርት ሚኒስትሯ አመላክተዋል።
ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ያለውን ሃገራዊ ፋይዳ በመረዳት ፕሮጀክቱ ተግባራቱን በፍጥነት ሊከውን እንደሚገባ የጠቆሙት የስራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ናቸው። የፕሮጀክቱን አፈፃፀም እና የቀጣይ እቅድ መሠረት በማድረግ የተሰጡትን ግብዓቶች አካትቶ ተግባራዊ እንዲሆን የጋራ መግባባት መደረሱን ከመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
