Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሀገሪቱን ልማትና እድገት ለማፋጠንና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የላቀ አስተዋፅዖ ማበርከቱ ተገለጸ
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት የሀገሪቱን ልማትና እድገት በማፋጠን የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ደረጃ በደረጃ ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረትና ርብርብ በመደገፍ ረገድ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ድርሻው የላቀ እንደሆነ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለፁ።
ዘርፉ እንደየአካባቢው ነባራዊ ሁኔታና እንደ ህብረተሰቡ ፍላጎት በተለይ በመንግስትና በህብረተሰቡ ያልተሸፈኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክፍተቶችን ለመሙላት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ ወጣቶችና ሴቶችን ጨምሮ የተለያዩ አካላትና ተቋማት በየዘርፉ በሚያከናውኗቸው ማናቸውም ጉዳዮች በያገባኛል ስሜት እንዲንቀሳቀሱና በማህበረሰቡ ዘንድ ጠቃሚ እሴቶችን፣ እውቀትና አሰራሮችን እንዲቀስሙ ማስቻሉን ገልፀዋል። በተጨማሪም ወጣቶች የእርስ በርስ ግንኙነታቸውንም እንዲያጠናክሩ፣ ከመንግስት መዋቅር ጋር እንዲቀራረቡና በየአካባቢያቸው እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎችን እንዲገነዘቡ አድርጓል ብለዋል።
በአገራቸው ሁለንተናዊ እድገትና የብልጽግና ጉዞ ላይም ደማቅ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ተጨማሪ ዕድል መፍጠር አስችሏል ሲሉ ጠቁመዋል። ሚኒስቴሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጡ በብሔራዊ ደረጃ ወጥነት እንዲኖረውና የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ለማስቻል ዘርፉ የሚመራበትን የአሰራር ማዕቀፍ በመቅረጽ፣ ስታንዳርድ በማውጣትና ትግበራውን በማስተባበርና በመከታተል ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
