Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሴክተር የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ቀረበ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሴክተር የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የ2018 በጀት ዓመት የተቋሙን ዕቅድ ከክልል እና ከተማ አስተዳደር ቢሮዎች ጋር በጋራ በማቀድ ለአፈፃፀም የሚያመች ውይይት በማካሄድ የተቋሙንና የፈፃሚውን አቅም የሚያጎለብቱ እንዲሁም ምቹ የስራ ከባቢ ለመፍጠርና አሰራርን ለማዘመን የሚያግዙ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። ሚኒስቴሩ በሩብ አመቱ በወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ ሴቶችና ወጣቶችን በማብቃት፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በመከላከልና ለጥቃት ተጎጂዎች የተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ረገድ ሰፊ ስራ መሰራቱን ክብርት ሚኒስትሯ ጠቁመዋል። እንዲሁም በአስቸጋሪ ሁኔታ ወስጥ ያሉ ህፃናትን በተለያዩ አማራጮች ለመደገፍ እና የገጠር ሴቶችን የመሬት ባለቤትነት መብት ለማረጋገጥ ጥረት መደረጉን አንስተዋል።
በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ምክንያት ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ሰፊ ሰራ መሰራቱን ተናግረዋል። የተቋማት አካቶ ትግበራ ውጤታማነት ለማሳደግ የሚያግዝ የተጠያቂነት ስርዓት ለመዘርጋት፣ የህፃናት ፓርላማዎችን ለማቋቋምና የታዳጊዎችን የተሳትፎ ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልፀው፥ በቀጣይም ሚኒስቴሩ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት በቁርጠኛነት እንደሚሰራ አስታውቀዋል። በዚህ ረገድ የችግሩን ስፋት በመገንዘብ ባለድርሻ አካላት የሚኒስቴሩን ጥረት እንዲደገፉና የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢው ዶ/ር ታደለ ቡራቃ በበኩላቸው፥ የሴቶችን፣ የህፃናትንና የወጣቶችን እንዲሁም የአረጋውያንን፣ የአካል ጉዳተኞችን እና ለችግር ተጋላጭ የህብረሰተሰብ ክፍሎችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራትን አድንቀዋል። ሆኖም ከተቋሙ ስፋት አንፃር ከሴክተር ያለፈ የተቀናጀ ስራን ስለሚጠይቅ በትብብር መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል። ቋሚ ኮሚቴው በሴክተሩ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤታማና ዜጎችም የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተጠናከረ የክትትል፣ ቁጥጥርና ድጋፍ ስራ ወደፊትም እንደሚሠራና አፈፃፀሙንም በየጊዜው እየገመገመ ግብረመልሰ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
