Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ሚኒስቴሩ ሴቶችና ወጣቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃት ያለሙና ማህበራዊ ልማትን የሚያጎለብቱ ተግባራትን ከኤኢ- ትሬድ ግሩፕ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሴቶችና ወጣቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃት ያለሙና ማህበራዊ ልማትን የሚያጎለብቱ ተግባራትን ከኤኢ- ትሬድ ግሩፕ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራረሟል።
ስምምነቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና የኤኢ- ትሬድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙላለም ስዩም ናቸው የተፈራረሙት። ስምምነቱ በዋነኛነት የሴቶችና ወጣቶችን አመለካከት በመለወጥ፣ የንግድ ስራ ክህሎት ስልጠናዎችን በመስጠትና በኢንተፕራይዞች በማደራጀት ወደ ንግድ ስራ እንዲገቡ የፋይናንስና የገበያ ትስስር በመፍጠር የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ ሰፊ ፕሮግራም መሆኑ ተገልጿል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ወቅት፥ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከተለያዩ የልማት አጋር አካላት ጋር በመተባበር የሴቶችና ወጣቶችን የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያግዙ የተለያዩ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶችን ነድፎ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ተናግረው ዛሬየተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ተደማሪ ውጤቶችን ለማስመዝገብ እንደሚያግዝ ተናግረዋል::
ስምምነቱ እንደሀገር በሴቶችና ወጣቶች የተጀመሩና አዳዲስ የንግድ እና የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጥ ፕሮግራሞች ዘላቂና ውጤታማ እንዲሆኑ ያግዛል ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ ለስኬታማ ትግበራ ተገቢው የክትትልና ድጋፍ ስራ ይሰራል ብለዋል። የኤኢ- ትሬድ ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ሙላለም ስዩም በበኩላቸው፥ ድርጅቱ በአፍሪካ ውስጥ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት መሰል ስራዎችን በመስራት በዘርፉ ያለውን የረጅም ጊዜ ልምድና ሰፊ እውቀትና የመተግበር አቅም በኢትዮጵያ እውን በማድረግ ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንና በጠንካራ አጋርነት ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ጋር ለመስራት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አረጋግጠዋል።
በቀጣይም ተቋማቱ በሴቶችና ወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማህበራዊ ልማትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በተመሳሳይ እየተገበሯቸው ካሉ ፕሮግራሞች ጋር በተቀናጀና ውጤታማነትን ከፍ በሚያደርግ ስልት በትብብር ለመስራትም የስራ ሃላፊዎቹ ተስማምተዋል።
