ፌዴራሊዝም ብዝኃነትን ባከበረ መልኩ ኅብረብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተገለጸ

‎20ኛውን የብሔር ብሄረሰቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ጋር በጋራ በመሆን ”ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ የሴቶችና ወጣቶች የአሰልጣኞች መድረክ ተካሂዷል።

‎‎በመድረኩ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ክቡር አቶ ጌታቸው በዳኔ በሀገሪቱ በየዓመቱ የሚከበረው የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን አብሮነትን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል። ‎እንደ ኢትዮጵያ ብዝሃን በሚንፀባረቅበት ሀገር ፌዴራሊዝም ብዝኃነትን ባከበረ መልኩ ኅብረብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡ ፌዴራሊዝም አንድ የፖለቲካ ሥርዓትን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በሕዝቦች ፍላጎትና ምርጫ ለመገንባት የሚያስችል አማራጭ መርህ መሆኑን ተናግረዋል። የስልጠናው ዓላማ በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ፌደራላዊ ሥርዓት ማእቀፍ የተገነባ ኅብረብሔራዊ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር የሚረዱ ግንዛቤዎችን በነደረጃው የሚገኙ ሴቶች እና ወጣቶች በዴሞክራሲ እና ፌዴራላዊ ሥርዓት ላይ ግንዛቤ እንዲያገኙ እና ለአገራችን አንድነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ መሆኑን ክቡር አቶ ጌታቸው በዳኔ ገልጸዋል።

‎በመድረኩ “ዲሞክራሲና የፌደራል ስርዓት በኢትዮጵያ፤ ተስፋዎቹ እና ተግዳሮቶቹ” በሚል ርዕስ በኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ በክቡር አቶ በላይ ወዲሻ አማካኝነት ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ክቡር አቶ በላይ ወዲሻ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል ሕዝቦች ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን እና ልምዶቻቸውን እርስ በርስ በመለዋወጥ አንድነት እንዲዳብር እና ስር እንዲሰድ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ሲከበር የቆየ መሆኑን ጠቅሰው በዓሉ ክልሎች እምቅ አቅማቸውን እና የኢንቨስትመንት አማራጮችን እንዲገልጡ ማስቻሉን አመላክተዋል፡፡

‎‎በመድኩ የሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ሴቶች እና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊዎች፣ የሴቶች እና ወጣቶች አደረጃጀት ተወካዮች፣ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽ/ቤት የሴቶች፣ ወጣቶች እና ሕፃናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ የሴቶች እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚነስቴር የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
‎

Please follow and like us: