ትውልዱን በሥነ ምግባር በማነጽ ለሙስና የማይበገር ዜጋ መፍጠር ይገባል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

‎ትውልዱን በሥነ ምግባር በማነጽ ለሙስና የማይበገር ዜጋ ለመፍጠር በትኩረት መስራት ያስፈልጋል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
‎‎22ኛው ዓለም አቀፍ የጸረ ሙስና ቀን በዛሬው ዕለት በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከበረ ነው፡፡‎
‎ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የምናየው ሀገራዊ ለውጥ እና እድገት የተመዘገበው የመደመር መንግሥት መንግሥታዊ ሙስናን አምርሮ የሚጠየፍ በመሆኑ ነው። ‎ብሔራዊ የጸረ ሙስና ኮሚቴ በማቋቋም ስለጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር እንዲሁም ዘላቂ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማመልከት የሚያስችሉ የንቅናቄ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል። ‎ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ሙስናን መከላከል የሚቻለው በሦስት መንገዶች ነው ብሎ እንደሚያምን አስረድተዋል፡፡ ‎የመጀመሪያው ራሱ መንግሥት ከመንግሥታዊ ሙስና ራሱን ነጻ ማድረግ የሚል ሲሆን÷ ይህም  ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ በመንግሥትነት ተደራጅቶ የሀገርንና የሕዝን ገንዘብ የመዝረፍ ልማድ ያስቆመ ነው ብለዋል።

‎ ‎በዚህ ረገድ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች እና የተመረጡ የሙያ ክፍሎች ሠራተኞች ሃብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የሚያስገድድ አዋጅ መተግበሩን አስታውሰዋል። ‎በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም መጀመሩን ጠቅሰው ÷ ይህም  እንደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዓይነት አዳዲስ የአሠራር መንገዶች እንዲዘረጉና ግልጽነትና ተጠያቂነትን በመፍጠር ሙስናን መከላከል ማስቻሉን አመልክተዋል። ‎የትውልድን ሥነ ምግባር መገንባት እና ለሙስና የማይበገር ዜጋ መፍጠርም ሌላኛው መንገድ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል:: ‎በተጨማሪም የሙስና መከላከል ተግባር በሦስት “መ” ዎች እንደሚጠቃለል አስገንዝበዋል፡፡‎1ኛው “መ” መገንባት ማለትም የትውልድን ሥነ ምግባር መገንባት ፤ 2ኛው “መ” መከላከል ይህም ተቋማዊ አሠራርን ማዘመን ሲሆን ÷ 3ኛው “መ” ደግሞ መከበር፣ ለሙስና ወንጀል ሕግ መከበር ሁሉም ቁርጠኛ መሆን አለበት የሚሉ እንደሆኑ አብራርተዋል።

Please follow and like us: