Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የምግብና የሥርዓተ-ምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ጤናማና አምራች ዜጋ የማፍራት ጉዳይ የሁሉም አጀንዳ ሆኖ መቀጠል እንደሚገባው ተገለፀ
ይህ የተገለፀው የያዳም ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ የስነምግብ ድጋፍን ለማጠናከር በተዘጋጀው የአድቮኬሲ መድረክ ላይ ነው።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንዳሉት የምግብና ስርዓተ ምግብ እጥረት እና ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም ህፃናት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚስተዋል ገልፀዋል። ትውልድን በተግባር እየፈተነ የሚገኘውንና በአብዛኛው ከአመጋገብ እና ከምግብ ደህንነትና ዋስት ጋር ተያይዞ እየተከሰተ ያለውን የመቀንጨር ችግር ለመፍታት ወሳኝ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ወደ ስራ በማስገባት ጠንካራ እርምጃዎችን እየተወሰደ ይገኛል ብለዋል።
መንግስት ከሚያደርገው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ጎን ለጎንም እንደ የያዳም ፋውንዴሽን በህፃናት እና በእናቶች ዙሪያ የሚሰሩ በርካታ የእነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች የተሟላ ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ የበኩላቸውን እገዛና ድጋፍ እያደረጉ ላሉ ተቋማት እውቅና ሰጥተዋል። ምንም እንኳ እስካሁን እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ቢሆንም ዛሬም የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑት ህፃናት ጤናማና የተሟላ አካላዊና አእምሯዊ ዕድገት መሠናክል ከሆኑ እንቅፋቶች መካከል አንዱ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት መሆኑን ጠቁመው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በጋራ መረባረብ ይጠበቅብናል ብለዋል።
በመሆኑም የምግብና የሥርዓተ-ምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ጤናማና አምራች ዜጋ የማፍራት ጉዳይ ለነገ የማይባል የሁላችንም አጀንዳ ሆኖ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል። የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የያዳም ፋውንዴሽን መስራች እና ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን እንደተናገሩት ለረጅም ጊዜ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመቅረፍ እና ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል የምናደርገው ትግል በርካታ ተግዳሮቶች የነበሩት መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ሰፊ እና ጠንካራ ብሔራዊ የምግብ እና የአመጋገብ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ እያደረገች ሲሆን ለአመጋገብ ስርዓትና እና ለስርዐተ ምግብ ልዩ ፕሮግራሞች ቅድሚያ እየሰጠች እንደምትገኝ ገልፀዋል።
የያዳም ፋውንዴሽንም ከፍተኛ ደረጃ ያለው የድጋፍ ፕሮጀክት እንደlarge scale food fortification (LSFF)፣ multiple micronutrient supplement (MMS )፣ Double-Fortified Salt (DFS)፣ የአመጋገብ አስተዳደር እና የፋይናንስ አቅርቦት ባሉ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ የአመጋገብ ዘርፎች ላይ ጠንካራ ምላሸ ሰጪ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል። በመድረኩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ክቡር አቶ መላኩ አለበል፣ የጤና ሚኒስትር ድኤታ ዶ/ር ደረጀ ድጉማ እና ባለድርሻና አጋር አካላት ተገኝተዋል።
