ዘንድሮ የሚከበረው የአለም አቀፉ የፍልሰት ቀንን አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

በአለም አቀፍ ደረጃ ለ25ኛ ጊዜ ሲሆን “ታላቁ ታሪኬ፣ ባህልና ልማት (My Great Story: Cultures and Development)” በሚል መሪ ቃል፣ እንዲሁም በሀገራችን ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ “ፍልሰተኞችን እናክብር፣ የወደፊት ህይወታቸውን በጋራ እንቅረፅ”(Honoring Migrants and Shaping a Shared Future) በሚል መሪ ቃል ታህሳስ 9 ቀን 2018 ዓ.ም (December 18, 2025 G.C.) በድምቀት ይከበራል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እ.ኤ.አ ዲሴምበር 2 ቀን 2000 ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት ዓለም አቀፍ የፍልሰት ቀን በየዓመቱ ዲሴምበር 18 ቀን እንዲከበር፣ የሚከበርበትም ዋና ዋና ምክንያቶች የፍልሰተኞችን አስተዋጽኦ ለመገንዘብ፣ ሰብአዊ መብቶቻቸውን ለማጉላት፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ፣ አስተማማኝና ፍትሐዊ የፍልሰት ሥርዓቶችን ለማስፋፋት፣ ለማድረግ እንደሆነ አመልክቷል፡፡ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ የፍልሰት ቀን ሲከበር ፍልሰት የዜጎችን ደህንነት እና ያላቸውን አስተዋፅኦ በሚያስከብር መልኩ መከናወን እንዳለበት ያምናል። የዘንድሮ አለም አቀፍ የፍልሰት ቀን ሲከበር ዜጎች ህጋዊ የሆነውን የፍልሰት ስርዓት እንዲመርጡ፣ በዚህም ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ማስገንዘብ ላይ ያተኮረ ይሆናል፡፡ በዓሉ ሕጋዊ ፍልሰትን በማስተማር፣ ተመላሾችን በማቋቋም እና በዘርፉ አዎንታዊ ለውጥ በማምጣት አስተዋጽኦ ላደረጉ ግለሰቦች፣ ተቋማትና ዲያስፖራዎች “የፍልሰት ሻምፒዮናዎች” እውቅና በመስጠትና በማበረታታት ለዜጎች አዎንታዊ የፍልሰት ታሪኮችን በማጋራት መደበኛ ፍልሰትን የሚስከትለውን ጉዳት በማጉላት ዜጎች መደበኛ የሆውን የፍልሰት መንገድ እንዲከተሉ መነሳሳት በመፍጠር ነው፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፉት ሦስት አመታት ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት፡-
👉የግንዛቤና የንቅናቄ ስራዎችን ከማከናወን አንጻር፤
👉መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ጎልቶ በሚታይባቸው ክልሎች ሀገራዊ የንቅናቄ መድረክ በማካሄድ ፣እንዲሁም የማህበረሰብ ወይይቶችን በማካሄድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በስፋት ተከናውነዋል ፡፡
👉የፍልሰት ተጎጂዎችን ከመደገፍና መልሶ ከማቋቋም አንጻር መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ወደ ተለያዩ ሀገራት ሄደው የተመለሱ ዜጎችን በተመለከተ ባለፉት ሦስት አመታት ድረስ ከከሳውዲ አረቢያ ፣ ከኦማን፣ ከየመን ፣ ከሱዳን፣ ከታንዛኒያ ፣ ከሞዛምቢክ፣ ከማይናማር በአየር መንገድና በድንበር በኩል በአጠቃላይ ከ500 ሺህ በላይ የፍልሰት ተጎጂዎችን በመቀበል የሥነ-ልቦናና የማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙና ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ስራም ተሰርቷል፡፡
👉 የትብብርና ቅንጅት ስራን በተመለከተ የትብብር ስራን በማጠናከር ረገድ በሰው መነገድ፣ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር መላክ ወንጀልን ለመከላከል እና የፍልሰት አስተዳደርን ለማጠናከር የሚያስችል የሆሳዕና የቃልኪዳን ሰነድ ጸደቆ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡
👉 ከተለያዩ አለም አቀፍ፣ አገር በቀል ከሆኑ ድርጅቶች ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈረም መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን የመከላከልና ተመላሽ ዜጎችን የመደገፍ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡

ከተደራሽነት አንፃር የመገናኛ ብዙኃን ሚና ጉልህ በመሆኑ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት አደጋዎች የሚያስከትሉት ጉዳት፣ እንዲሁም ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ሊያገኙዋቸውን የሚችሉትን አስተማማኝ አገልግሎት በስፋትና በተከታታይ በማስተዋወቅ ግንዛቤ በመፍጠር ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥሪ ያቀርባል።

Please follow and like us: