Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
በግብርና እና ጤና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት ላይ የተከናወነው የአካቶ ትግበራ ምዘና ውጤት ይፋ ሆነ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካቶ ትግበራ መመዘኛ ማዕቀፍን (Inclusive Leveling Tool) መሰረት በማድረግ በ22 የግብርና እና የጤና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት ላይ ያከናወነውን የምዘና ውጤት ይፋ አደረገ ። በዕለቱም ከፍተኛ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማት የእውቅና መርሃ ግብር ተካሂዷል ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ ምዘናው የተካሄደው ሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን በየዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተቋማቱ ያላቸውን ዝግጁነት ለመለካት ነው ። በምዘናው ሂደት የታዩ ዋና ዋና ነጥቦች መካከል በእቅድና በበጀት ዝግጅት ወቅት የስርዓተ-ጾታና የሌሎች ተጋላጭ ክፍሎችን ጉዳይ አካቶ በመስራት ረገድ ሰፊ ክፍተቶችና አበረታች ጥንካሬዎች መኖራቸውንና መለየታቸውን ጠቁመዋል። ምንም እንኳን በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 መሰረት መልካም ጅምሮች ቢኖሩም፣ የአካቶ ትግበራው አሁንም በሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረሱን ገልፀዋል ::
ለአፈጻጸም መዳከም በምክንያትነት የተጠቀሱት የቅንጅታዊ አሰራር ጉድለት፣ የአመራር ቁርጠኝነት ማነስ፣ የባለሙያ ክህሎት ማነስ እና የተጠያቂነት ስርዓት አለመጠናከር መሆናቸውንም ተናግረዋል። ሚኒስትሯ አክለውም፣ ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው ተቋማት ከዚህ መድረክ ልምድ በመውሰድ አሰራራቸውን ማሻሻል እንዳለባቸው አሳስበዋል ። በቀጣይ ማሻሻያ በማያደርጉ ተቋማት ላይ የተጠያቂነት ስርዓት እንደሚዘረጋም አስገንዝበዋል ።
