Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ወጣቶች ራሳቸውን በኢኮኖሚ ማብቃት እንዲችሉና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የሚያስችል ክህሎት መር የፕሮግራም ትግበራ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ::
ይህ የተገለፀው ከኮሪያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (KOICA) ከተ.መ.ድ የስነ-ህዝብ ድርጅት (UNFPA) እና የ.ተ.መ.ድ የስደተኞች ድርጅት ( UNHCR) በተገኘ የ1.6 ቢሊዮን ብርየገንዘብ ድጋፍ በአፋር እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በመፈናቀል እና በማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለተጎዱ ማኅበረሰቦች አጠቃላይ እና ስትራቴጂያዊ ምላሽ ለመስጠት ይፋ የተደረገውን ፕሮጀክት ወደ አፈፃፀም ለመግባት በተዘጋጀው የአብይ ኮሚቴ ውይይት ወቅት ነው።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) አንደገለፁት ከጊዚያዊ እርዳታ ባለፈ ወጣቶች ራሳቸውን በኢኮኖሚ ማብቃት እንዲችሉና በዘላቂነት መቋቋም የሚያስችል ክህሎት ማስጨበጥ ላይ በትኩረት መስራት የመንግስት ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን ጠቁመው ይህ ፕሮጀክትም ዋነኛ የትኩረት መስክ እንደሆነ ተናግረዋል። በዚህ ፕሮጀክት ከ60 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን ማብቃት ፣ተቋማዊ አቅምን መገንባት፣ የመንግስት ተቋማት የወጣቶች ስነ-ተዋልዶ ጤና እና ከፆታ ጋር የተያያዙ ጥቃቶችን (GBV) የመከላከል አቅምን ማሣደግ ራስን መቻልን ማበረታት ላይ እንደሚያተኩር ገልፀዋል ።

ኮሚቴው ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የፕሮጀክቱን አፈጻጸም የመቆጣጠር፣ ግልፅነትን የማረጋገጥ እና የሚያጋጥሙ እንቅፋቶችን የመፍታት ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው በዕለቱ ተጠቁሟል ። በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አስተባባሪነት ከኮሪያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (KOICA) እና ከተ.መ.ድ የስነ-ህዝብ ድርጅት (UNFPA) የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበረው ፕሮጀክት በስደተኞችና ስደት ተመላሾች አገልግሎት ጋር በመቀናጀት በአፋር እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በመፈናቀል እና በማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለተጎዱ ማኅበረሰቦች አጠቃላይ እና ስትራቴጂያዊ ምላሽ ለመስጠት ያለመ መሆኑ ይታወሳል።
