የአፋሪካ ቀንድ የወጣቶች ፎረም የፊታችን ቅዳሜ በድሬዳዋ አስተዳደር ይካሄዳል።

“ለዘላቂ ሰላም ግንባታና የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች ወጣት መር ጥረቶችን ማበረታታት /”Empowering Youth Led Efforts for Sustainable Peace Building and Climate Action”/በሚል መሪቃል የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የሚሳተፉበት የወጣቶች ፎረም በድሬዳዋ አስተዳደር እንደሚካሄድ ተገልጿል። የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከድሬዳዋ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን እና ከድሬዳዋ አስተዳደር የወጣቶች ምክር ቤት ጋራ በመሆን ስለ ፎረሙ ዝግጅት አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

‎በመግለጫው ላይ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር የወጣቶች ተሳትፎ አደረጃጀትና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ የሆኑት አቶ አድነው አበራ፥ በሀገሪቱ ዓርዓያ የሚሆኑና ጥሩ ወጣቶች እየፈሩ መሆኑን ገልፀዋል። ይህ ደግሞ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ በጎ ለውጦችን እንደሚያመጣም ጠቅሰው በዚህ መድረክ የኢትዮጵያውያን ወጣቶች አቅም ከፍ ብሎ መታየት አለበት ብለዋል። አቶ አድነው አያይዘውም ፎረሙ ከጥር 29 ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን አራት ዋና ዋና አጀንዳዎች እንደሚኖሩት አክለዋል። ወቅታዊ ጉዳዮች፣ የሰላም ጉዳይ፣የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ እና የባህር በር ተደራሽነትን የመሳሰሉ ጉዳዮች በስፋት በፎረሙ ላይ የሚነሱ አጀንዳዎች ናቸው ሲሉ አብራርተዋል።

‎የድሬዳዋ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሸነር ካሊድ መሀመድ በአስተዳደሩ የሚካሄደው ይህ አህጉራዊ ፎረም በአይነቱ ለየት ያለ መሆኑን ገልፀው በፎረሙ ላይ ወጣቶች በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ፤ ለአብነትም ስለ አየር ንብረት ለውጥ፣ ስለ ቀጠናዊ ሰላም በስፋት ይወያያሉ ብለዋል። ኮሚሽነሩ አክለውም እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ በርካታ ተምሳሌታዊና ተሞክሮ ሊሆኑ የሚችሉ ሥራዎችን በመስራት ላይ እንደምትገኝ ገልፀው ድሬዳዋ ላይም ከሰላም በዘለለ ከአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ከመከላከል አኳያ ጥሩ የሚባሉ ተሞክሮዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። እነዚህን ተሞክሮዎች ደግሞ ወጣቱ ማስተዋወቅ ያለበት በመሆኑ፥ ወጣቱ በዚህ ረገድ የራሱን አሻራ ማሳረፍ አለበት ብለዋል። ‎የድሬዳዋ አስተዳደር የወጣቶች ምክርቤት ፕሬዚዳንት ወጣት ሀሚድ አብደላህ በበኩሉ ለፎረሙ እንደ አስተዳደር በቂ የሚባል ዝግጅት እንደተደረገ ገልፆ ፎረሙ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር እንደሚያስችል ገልጿል።
‎
‎በፎረሙ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከጅቡቲ፣ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳን እና ከሶማሌ ላንድ የተወጣጡ ወጣቶች እንደሚሳተፉ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተጠቁሟል።

Please follow and like us: