7ኛው ሀገራዊ ምርጫ አካታችና ሰላማዊ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

በ7ኛው ጠቅላላ ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ የሴቶች፣ ወጣቶችና የማህበራዊ አካታችነት በተመለከተ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።

‎‎በምክክር መድረኩ የሁሉም ክልል የሴቾችና ማህበራዊ ሴክተር ሃላፊዎች፣ የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የተለያዩ አደረጃጀት ተወካዮች እየተሳተፉ ነው። በመድረኩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ የዜጎች ተሳትፎ የሥርዓቱ መገለጫ ብቻ ሳይሆን ለፍትሃዊ ውክልና እና ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ ምሰሶ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል። ‎ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞችን፣ አረጋውያን እና አኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በምርጫ ማሳተፍ ለሀገራዊ መረጋጋትና ለሰላም፣ ለጠንካራ ሀገረመንግስት ግንባታ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አንስተዋል። ‎ባለፉት ዓመታት የዜጎች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ተስፋ ሰጪ እድገቶች መመዝገብ ችሏል ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ በተለይም የሴቶች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የነበራቸው ውክልና ከ1987 ዓ.ም ከነበረበት 2.7% በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ወደ 41.2% ማደጉ ታሪካዊ ስኬት መሆኑን ገልፀዋል። በ7ኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ውስጥም የሴቶች፣ የወጣቶች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የአረጋውያን እና ሌሎች ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተሳትፎ ትርጉም ባለው መልኩ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

‎‎ምርጫው አካታች እንዲሁም ነፃ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆንና በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም ሚናቸውን በሚገባ እንዲወጡ ሲሉ ተናግረዋል። ‎ሚኒስቴሩ እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች በመምረጥና በመመረጥ፣ በማስመረጥና በታዛቢነት በንቃት እንዲሳተፉና ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል። ‎የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ክቡር አቶ ተስፋዬ ነዋይ በበኩላቸው፥ ሀገራችን ኢትዮጵያ 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሰፊ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን ገልፀዋል። ምርጫው ማህበራዊ አካታችና ስኬታማ ለማድረግ የህግ ማዕቀፎችን የማዘጋጀት፣ የዲጂታል ምዝገባ ስርዓት የመዘርጋት፣ የፋይናንስ አሰራር የማበጀት እና ምቹ መደላደል ለመፍጠር የሚያግዙ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል። የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሒክማ ከይሬዲን ሀገራዊ ምርጫውን አስመልክቶ የውይይት መነሻ ሰነድ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።

Please follow and like us: