ፖፑሌሽን ሰርቪስስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጲያ (PSI Ethiopia) የተሰኘው አለም አቀፍ ተቋም የሴቶች እና ወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ትብብር እና ድጋፉን እንደሚያጠናክር አስታወቀ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በፖፑሌሽን ሰርቪስስ ኢንተርናሽናል የግሎባል ሄልዝ ዳይሬክተር ሚስተር ክርስቶፈር ሎረንሶ እና በድርጅቱ የኢትዮጵያ ፕሮግራም ሃላፊዎችን ትብብርን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ መክረዋል።

‎ውይይቱ በዋነኝነት በገጠር ለሚኖሩ ሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚነት የሚያግዙ ምቹ እድሎችን መፍጠር በተለይም ደግሞ በግብርናው ዘርፍ ያላቸውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማስፋት እንዲሁም ክህሎትን፣ የዲጂታል መፍትሔዎችንና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን የበለጠ ማጠናከር ላይ ያተኮረ ነው። ‎ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ወቅት፥ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ሴቶችና ወጣቶችን ዘላቂ እና አካታች በሆነ መንገድ ያላቸውን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን በቅንጅት እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል። በተጠቀሱት ዘርፎችም ከፒ ኤስ አይ (PSI) ጋር በትብብር መስራቱ የተቀረጹት ፕሮግራሞችን ለማሳካት ያግዛታል ብለዋል።

ሚስተር ክርስቶፈር ሎረንሶ በበኩላቸው፥ ፒ ኤስ አይ በአፍላ ወጣቶች፣ በወጣት ሴቶችና ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ጤና፣ የኑሮ መተዳደሪያ፣ ጥበቃና ዲጂታል ፈጠራ ላይ ያተኮረ የተቀናጀ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ሴቶች እና ወጣቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያም በተጠቀሱት የትብብር መስኮች ያለውን ሰፊ ልምድ ለማካፈል እና ድጋፉን ለማጠናከር ድርጅቱ ፍላጎት እንዳለው አስታወቀዋል።

Please follow and like us: