‎7ኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ወጣቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

7ኛው አገራዊ ምርጫ ፍትሃዊና ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ወጣቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ ጥሪ አቀረቡ።

‎‎መጪው ሀገራዊ ምርጫን አስመልክቶ “የወጣቶች ድምፅና ተሳትፎ ለሰላምና ለዴሞክራሲ” በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። ‎የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፥ ከሀገሪቱ ህዝብ ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጋው ወጣቱ ትውልድ የሀገሪቱ ተስፋና ዋነኛ የለውጥ ሞተር መሆኑን ጠቅሰዋል። የታመቀ እውቀትና ጉልበት ባለቤት የሆኑት ወጣቶች ለሀገሪቱ ሰላም ብሎም የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞ መፋጠን ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል። ‎ቀጣይ የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫም ሰላማዊ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድና በስኬት እንዲጠናቀቅ ወጣቶች ብስለትን በተላበሰና በባለቤትነት ስሜት በንቃት እንዲሳተፉና የሰላም አምባሳደር መሆናቸውንም ለዓለም እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል።

‎‎ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወጣቶችን ጨምሮ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ለችግር ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች እኩልና አካታች ያደረገ የምርጫ ተሳትፎ እንዲኖር ለማስቻል ከምርጫ ቦርድና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሆነ ተናግረዋል። ‎በመርሐግብሩ ላይ የፌዴራልና የክልል ቢሮ ኃላፊዎች፣ የወጣት ምክር ቤት አመራሮች እንዲሁም የማኅበራት፣ የሊግ እና የፌዴሬሽን አደረጃጀት ተወካዮች ተገኝተዋል።
‎

Please follow and like us: