‎የሰው ልጅን ክብር ማስቀደም ከቻልን፣ ግጭቶችን በውይይትና በፍቅር መፍታት እንችላለን – ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ

“እኔ በሰውነቴ ከማንም አልበልጥም፤ አላንስም! እርስዎስ?” በሚል መሪ ሃሳብ በሰላም እሴት ግንባታ ላይ ያተኮረ ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት የተሳተፉበት ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

‎‎በመክፈቻ መርሐግብሩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደተናገሩት፤ ሰው በሰውነቱ እኩል መሆኑን የዘነጋ ትውልድ በቀላሉ ለጥላቻና ለግጭት ይጋለጣል ብለዋል። ‎ሀገራችን ለምትገኝበት ውስብስብ ችግር አንዱና ዋነኛው ምክንያት የሰው ልጅ ለሰው ልጅ ያለው ክብር መሸርሸሩ እና በሰዎች ልቦና ውስጥ ያለው የተዛባ አመለካከት መሆኑን ገልፀዋል። ‎እኔ ከሌላው በልጣለው፤ ሌላው ከኔ ያንሳል የሚሉ እሳቤዎች በሀገሪቱ ግጭቶች እንዳይበርዱ ማድረጋቸውን የገለፁት ክብርት ሚኒስትር ኤርጎጌ፥ የሰው ልጅን ክብር ማስቀደም ከቻልን ግጭቶችን በውይይትና በፍቅር ማቆም ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል። የሰላም ጉዳይ ሁሉንም የሚመለከት እንደመሆኑ በሰላም ዙሪያ በጋራ መቆም ያስፈልጋል ብለዋል። ‎ስለሰው ልጆች ሰላምና አንድነት-ክብርና እኩልነት በሁሉም የሃይማኖት አስተምህሮዎች ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው “እኔ በሰውነቴ ከማንም አልበልጥም፤ አላንስም” የሚለው አስተሳሰብ በየደረጃው እንዲሰርፅም ሁሉም ሃላፊነቱን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።

‎የተሳሳተ አስተሳሰብ የሚያሰርፁ፣ ግጭትን የሚሰብኩ፣ ልዩነትን የሚያጎሉና ሰብአዊ ክብርን የሚያዋርዱ ድርጊቶችን ከቤተሰብ ጀምሮ ሁሉም በጋራ እንዲገስፅም ጥሪ አቅርበዋል። ሚኒስቴሩ ከሃይማኖት ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር አስተሳሰቡ እስከታች እንዲሰርፅ ሰፊ ማህበረሰባዊ ንቅናቄ እንፈጥራለን ብለዋል። ‎በመድረኩ የተሳተፉ የሃይማኖት አባቶች የሰው ልጅን ሰላም ለማፅናት፣ ማንነቱንና ክብሩን ወደ ነበረበት ከፍታ ለመመለስ የሚከናወኑ ተግባራትን በጋራ ለመስራት ቃል ገብተዋል።

Please follow and like us: