በዓለም የውሃ ቀን 2026 ላይ የጾታ እኩልነትን ያገናዘበ የውሃ አቅርቦት እንዲረጋገጥ ጥሪ ቀረበ

ጥሪው የቀረበው በሲሲአርዲኤ (CCRDA) የውሃና ሳኒቴሽን ፎረም በተዘጋጀው የ2026 ዓለም አቀፍ የውሃ ቀን አከባበር ላይ ነው።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዕለቱ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት፥ የውሃ አቅርቦት ሰብአዊ መብትን፣ ክብርን እና እኩልነትን የማረጋገጥ ጉዳይ በመሆኑ በዓለም የውሀ ቀን የፆታ እኩልነትን ያገናዘበ የውሀ አቅርቦት እንዲረጋገጥ ጥሪ አቅርበዋል። የዘንድሮው ዓለም አቀፍ መሪ ቃል “Water and Gender” የሚል ሲሆን ይህም በውሃ እጥረት ምክንያት ሴቶችና ታዳጊ ሴቶች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በተለይም የትምህርትና የኢኮኖሚ አስተዋጽዖዎቻቸውን እንደሚገድብ ገልፀዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በዘርፉ ያለውን ችግር ለመቅረፍ እና የወር አበባ ንፅህና አጠባበቅን ጨምሮ የሴቶችን ፍላጎት ያገናዘበ የተቀናጀ የውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኑን ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም ሴቶች በውሃ አስተዳደር ላይ በውሳኔ ሰጪነት እንዲሳተፉ እና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጫና ለመቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል። ሲሲአርዲኤን ጨምሮ የሲቪክ ማህበራት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አድንቀው ማንንም ወደኋላ የማይተው ስርአት ለመገንባት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሰሩ አሳስበዋል።

Please follow and like us: