በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶችና የወጣቶች ሚና የጎላ ነበር- የኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን በኢትዮጵያ የተካሄደውን 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ ያዘጋጀውን የመጀመሪያ ደረጃ የምርጫ ምልከታ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

በጥምረት የተሰማሩት የኢጋድ ታዛቢዎች በምርጫው ዕለት የነበረውን የሂደት ሁኔታ፣ የመራጮችን ተሳትፎ እና አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱን  አስመልክቶ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል። ታዛቢዎች በዕለቱ ቀኑን ሙሉ ከፍተኛ የመራጮች ተሳትፎ እንደነበርና በብዙ የምርጫ ጣቢያዎች ረጃጀም ሰልፎች መታየታቸውን ገልጸዋል። እንደ ሪፖርቱ መግለጫ፥ በምርጫ ጣቢያዎች የታየው የመራጮች ስብጥር በሰዓታት ልዩነት የተለያየ መልክ ነበረው ብለዋል። በዘንድሮው ምርጫ የሴቶች ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ ጎልቶ መታየቱን የገለጸው የኢጋድ መግለጫ፤ ሴቶች በምርጫ አስፈጻሚነት፣ በእጩነት፣ በፓርቲ ወኪልነት እና በታዛቢነት ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውን አረጋግጧል።

ሂደቱን ለመከታተል የሁኔታዎች መግለጫ ክፍል ያቋቋሙ በርካታ ተቋማት የነበሩ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ታዛቢዎች፣ ታዛቢ ቡድኑ በጎበኛቸው አብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው እንደነበር አመላክተዋል። በተጨማሪም የሴቶችን ተሳትፎ ለመከታተልና ለመደገፍ፤ የኢትዮጵያ ሴት ጠበቆች ማህበር፤ትምራን የተሰኘው በሴቶች የሚመራ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት፣ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ታዛቢዎችን ካሰማሩ ድርጅቶች መካከል  በዋናነት ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች በምርጫው ሂደት ውስጥ በነበራቸው ሚና ታዛቢ ቡድኑ ልዩ ምስጋና አቅርቧል። ወጣቶቹ በምርጫ አስፈጻሚነት፣ በእጩነት፣ በፓርቲ ወኪልነት፣ በታዛቢነት፣ በበጎ ፈቃደኝነት እና በሁኔታዎች መግለጫ ክፍል ሰራተኛነት ተሰማርተው የታዩ ሲሆን፤ በተለይም በምርጫ ጣቢያዎች ዙሪያ መራጮችን በመምራት፣ ወዴት መሄድ እንዳለባቸው በማሳየት እና በማስተናገድ ረገድ ከፍተኛ ስራ ማከናወናቸው ተገልጿል።

ታዛቢዎቹ “እኛ ታዛቢዎች ነን” የሚል ግልጽ መለያ ለብሰው በደስታ የተቀበሏቸውን የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ታዛቢዎችን ሚና አድንቀዋል ሲል ኤ ኤም ኤን ዘግቧል።

Please follow and like us: