‎የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት በሩሲያ ፌዴሬሽን ከሚገኘው All-Russian public-state movement of children and youth, “Movement of the first” ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ትብብርን ለማስፋፋት ትልቅ ምዕራፍ እንደሚከፍት ታምኖበታል።

‎ስምምነቱን የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ፉአድ ገናና የAll-Russian public-state movement of children and youth, “Movement of the first” የቦርድ ሊቀመንበር አርተር ኦርሎቭ በሩሲያ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ገነት ተሾመ በተገኙበት ተፈራርመዋል። ‎ይህ አጋርነት ኢትዮጵያና ሩሲያ  በወጣቶች መሪነት ልማት፣ በትምህርትና በባህል ልውውጥ፣ በስራ ፈጠራ፣ በክህሎት ልማት፣ በሰላም ግንባታ፣ በቱሪዝም ልውውጥ፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነትና በጋራ የወጣት ፕሮግራሞች ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸው ስለመሆኑ ተመላክቷል። ‎በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ  ላይ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ፉአድ ገና ባደረጉት ንግግር የወጣቶች ዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ትብብር ወጣቶችን ለማበረታታትና መጪው ትውልድ ለዓለም አቀፍ ልማት ንቁ አስተዋፅዖ እንዲያደርግ ለማዘጋጀት አበርክቶው የጎላ ነው ብለዋል።

‎‎‎ዓለም ከምንጊዜውም በላይ እየተቆራኘ ባለበት በዚህ ወቅት፤ በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግና ዓለም አቀፍ ትብብሮችን መፍጠር ዘላቂ አጋርነትና የተሻለ ነገን ለመገንባት ያግዛል ሲሉም ተናግረዋል። ‎የመግባቢያ ስምምነቱ በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል ያለውን የወጣቶች ግንኙነት ለማስፋፋትና በሁለቱ ሀገራት ለሚገኙ ወጣቶች ዘላቂ እድሎችን ለመፍጠር እንደሚያስችል በመድረኩ መገለፁን ምክር ቤቱ አስታውቋል። ‎የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ዓለም አቀፍ ግንኙነቱን በማስፋትና በማጠናከርና የኢትዮጵያ ወጣቶች በዓለም መድረክ ላይ ተወክለው በሁለንተናዊ መልኩ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል ።

Please follow and like us: