Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
ሙስናና ብልሹ አሰራርን ማስወገድ የዜጎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተገለፀ
ይህ የተገለፀው ለተቋሙ ከፍተኛ እንዲሁም መካከለኛ አመራሮች የሚሰጠው የሥነ-ምግባር፣ የፀረ-ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር፣ የለውጥ አመራርና የውስጥ ኦዲት አገልግሎት ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ ነው።
በስልጠና መድረኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ማንኛውም የመንግስት ተቋም የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት መወጣት የሚችለው ማህበረሰቡን በታማኝነትና በቅንነት ሲያገልግልና የተቋሙን ሀብት በቁጠባና በውጤታማነት ሲጠቀም ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል አያይዘውም በየደረጃው የሚገኘው አመራር ራሱን ወደ ውስጥ በመመልከትና ክፍተቶቹን ፈጥኖ በማረም ለሕዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል በሙሉ ቁርጠኝነት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስበዋል። የመንግስት አገልግሎት ሪፎርም በዋናነት የህዝብን እርካታ ከፍ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት የትኛውም ተቋም በትላንትናው የቢሮክራሲ አስተሳሰብ ዛሬ ላይ ውጤታማ ሊሆን ስለማይችል ሙስናና ብልሹ አሰራርን ማስወገድ የዜጎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልፀዋል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአሰራር ስርዓትን ለመዘርጋትና ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም፣ አሁንም በአመራሩና በፈጻሚው ላይ የሚስተዋሉ የአመለካከትና የክህሎት ክፍተቶችን መሙላት የግድ ይላል። ሰልጣኞች በስልጠናው ያገኙትን እውቀት በስራ ክፍላቸው ላሉ ኃላፊዎችና ፈጻሚዎች በማካፈል፣ ተቋሙን ከሙስና የጸዳ፣ ተገልጋይን የሚያረካና ሀብትን በቁጠባ የሚጠቀም በማድረግ የዘላቂ ማህበራዊ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ስልጠናው ከሥነ ምግባር ግንባታ፣ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ከመከላከል አንፃር ያለዉን ጠቀሜታና የስልጠናውን አላማ በየደረጃዉ ላሉ የተቋሙ አመራሮች የስነ-ምግባር ግድፈቶችን መከላከል፣ የጠራ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል የማስወገጃ ስልት በማዘጋጀት ግልጽ፣ቀልጣፋ ፣ውጤታማና በተጠያቂነት ላይ የተመሰረተ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ግብ ተኮር ስልጠና መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል ።
