የሚኒስቴሩ አመራርና ሠራተኞች በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ለመትከል የተያዘውን የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ለማሳካት ከ5ሺህ በላይ ችግኞችን ተክለዋል

,የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች፣ ሠራተኞች፣ ታዳጊ ህፃናት፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እና ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል ሀገራዊ ጥሪን በመቀላቀል ከአምስት ሺህ በላይ ችግኞችን በጋራ ተክለዋል።

በዕለቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለፁት የተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሀገሪቱ የጀመረችውን የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም እና የደን ሽፋን የማሳደግ እንቅስቃሴ አካል ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም እያደገ የመጣው የደን ሽፋን ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል። የህፃናት እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ልዩ ድምቀት የሰጠው የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩ ህፃናት በችግኝ ተከላው ላይ በንቃት በመሳተፋቸው የተፈጥሮ አካባቢን የመንከባከብ ባህል ለተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል።

በተጨማሪም ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉትን ተክሎች መንከባከብ እና ማሳደግ ለነገዋ ኢትዮጵያ ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የማህበረሰብ ተሳትፎን ያማከሉ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችንና እና የማህበራዊ ደህንነትን የማረጋገጥ ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።

በዕለቱ 7 የደን አይነቶች የተተከሉ ሲሆን ከ200 በላይ በጎ ፈቃድኛ ወጣቶች፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽን እና የሲቪክ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል።

Please follow and like us: