ሚኒስቴሩ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥን ቀዳሚ ተግባር በማድረግ ዘላቂና ዘመኑን የዋጁ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል- ክብርት ሙና አህመድ

ይህ የተገለፀው “ብዝሀ የወጣቶች እውቀት ለጋራ ትልም” በሚል መሪ ቃል ከኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመቀናጀት በጅማ ከተማ በመካሄድ ላይ ባለው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ነው።
የሚኒስቴሩ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ እንደገለፁት፥ ሚኒስቴሩ ወጣቶች የሀገር ሀብት ፈጣሪዎች እና የኢኮኖሚ ዋና አቀጣጣይ እንደመሆናቸው የወጣቶችን እምቅ አቅም ለሀገር ብልጽግና ማዋል ይቻል ዘንድ በከተማና በገጠር የሚገኙ ወጣቶችን በስራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርጉ፣ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ አቅርቦቶችን የሚያመቻቹ ሰፊ ስራዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል። በወጣቶች ዘርፍ በዋና ዋና የትኩረት መስኮችም የወጣቶች ስብእናና ስነ-ምግባር ግንባታ፦ ጠንካራ እና አዎንታዊ ትውልድ ለመገንባት የሚያስችል ብሔራዊ የወጣቶች ስነ-ምግባር እና የአካል ብቃት ስትራቴጂ በማዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መግባቱን ገልፀዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶቻችን እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን ሳይሰስቱ ለሀገራቸው በመስጠት ላይ ይገኛሉ። ይህ አገልግሎት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከመስጠቱ ባለፈ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት መንፈስ በማዳበር ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ላይ እንዳለ ጠቁመዋል። ከሰላምና ደህንነት አንፃርም ወጣቱ የሰላም ግንባታ ግንባር ቀደም ባለቤት በመሆን ወጣቶችን የግጭቶች መጠቀሚያ የሚያደርገው የቆየ አካሄድ ሙሉ በሙሉ መለወጥ አንዳለበት ጠቁመው ወጣቱ የሰላም አስከባሪ፣ የውይይትና የምክክር መድረክ መሪ እና የሀገር ግንባታ ዋና ባለቤት እንዲሆን መዋቅራዊ መፍትሔዎች ተቀርፀው እየተተገበሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በቀጣይም የወጣቶችን የውሳኔ ሰጪነትና ተሳትፎና በዲጂታል ዘመን የወጣቶች የፈጠራ ክህሎት በማሳደግ ለሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት በማዋል ብቃት ያለው የሰው ኃይል በማፍራት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸውወጣቶችን በማብቃት ህበረትና አንድነታቸውን በማጠናከር የሀገርን ብልጽግና ማረጋገጥ ያስችላል ያሉ ሲሆን በዞኑም ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሯል ነው ያሉት።
በዕለቱም በወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ የኤግዚብሽንና ባዛር አውደርዕይ የተካሄደ ሲሆን በተጨማሪም የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲሁም ስብዕና ልማት ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
Please follow and like us: