የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር በትውልድ ግንባታ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር በትውልድ ግንባታና በሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
በሚኒስቴሩ የወጣቶች ብሔራዊ አገልግሎትና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስፋፊያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አብይ ኃይለመለኮት ለኢዜአ እንዳሉት፤ የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ በየዓመቱ ሀገራዊ ባህል እየሆነ መትቷል።
መርሃ ግብሩ ወጣቶች ዕውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን ለማኅበረሰባቸው በሚጠቅሙ የልማት ሥራዎች የሚያውሉበትን ጠቃሚ ዕድል እንደፈጠረም አስረድተዋል። ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት ጀምሮ የበጎ ፈቃድ ባህል በመጠናከሩ የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች በሰፊው እየተከናወኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በሰብዓዊ ድጋፍ፣ በትምህርትና በሌሎች የበጎ ፈቃድ መስኮች በመሳተፍ ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሆነ ገልጸዋል። እነዚህ ተግባራትም አቅመ ደካሞችን፣ የሀገር ባለውለታዎችን፣ አካል ጉዳተኞችንና አረጋውያንን በመደገፍ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጋላጭነታቸውን እየቀነሱ የተሻለ ኑሮ እንዲመሩ እያስቻሉ መሆኑንም አክለዋል።
የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገርም በትውልድ ግንባታና በሀገራዊ አንድነት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስክ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን የመደገፍ ልምዳቸውን በማሳደግ ተሳትፏቸውን እያጎለበቱ መሆኑን ገልጸዋል።
ተሳታፊ ወጣቶች ልምድና ባህላቸውን በመጋራት የኢትዮጵያን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የሚያጠናክር የትውልድ ስብዕና ግንባታንና የሀገር ፍቅር ስሜትን እያጎለበቱ መሆኑን አስረድተዋል። በተያዘው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ 25 ሚሊዮን ወጣቶችን በማሳተፍ ከ53 ሚሊዮን በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ ተቀምጧል።
ይህንን ግብ ለማሳካትም ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ ወደ ተግባር መግባታቸውን ገልጸዋል።
በመጨረሻም የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ባለድርሻ ተቋማትና አጋር አካላት የተያዘውን ግብ ለማሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
Please follow and like us: